እየሩሳሌም ነጋሽ የቀድሞ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋች እና አምበል ነበረች። እንዲሁም የእንቁዋ ታብራ ሴቶችን የሚያነቃ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ናት።
እየሩሳሌም የገጠማት የራስዋን የጨቅላ ህፃን ማጣት (stillbirth) በድፍረት ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ሚዲያ በመናገር ለብዙዎች ድምፅ እና ብርታት ሆናለች። ካለፈችበት አሰቃቂ የአካልና የስሜት ህመም ተነስታ ሩት የመደጋገፊያ ቡድን (Ruth Support Group) በማቋቋም የፅንስ መጨንገፍ እና የጨቅላ ህፃናት ሞት የገጠማቸውን እናቶች ቦታ አግኝተው ሀዘናቸውን እንዲወጡና ከቁስላቸው እንዲድኑ ሙያዊ የስነ አዕምሮ ድጋፍ እንዲያገኙ ታደርጋለች።
በዚህ ብሎግ እየሩሳሌም ልቧን ከፍታ የወሊድ ታሪኳን ታካፍለናለች። ይህ የእየሩሳሌም ታሪክ ብዙ እናቶች የሚያልፉበት ነገር ግን በማህበረሰባች ተቀባይነት ማጣት ደፍረው የማያወሩት የጨቅላ ህፃን ሞት (stillbirth) የተጋፈጠችበት ታሪኳ ነው።
ስታነቡት ከባባድ አሳዛኝ ወይም አስጨናቂ ስሜቶች ሊቀሰቅስ እንሚችል ማስጠንቀቂያ ለመስጠት እንወዳለን። በአመቺ ቦታ ይነበብ።
“ምጡን እርሺው ፤ ልጁን አንሺው”
…. ማንሳት ያልተቻለ ‘ለታስ?
በእየሩሳሌም ነጋሽ
ሁልጊዜም ባይሆን አንዳንዴ በህይወታችን ፍጹም ካልገመትነውና ካልጠበቅነው ቦታ እንድንገኝ ይሆናል። በርግጥ ለእኛ አጋጣሚ ቢመስልም ነገሩ በአምላክ ዘንድ የታወቀ የተወሰነ ለመሆኑ ጥርጣሬ የለኝም። (አሁን ላይ ሆኜ ሳየው)
እናማ ህዳር 21/2014 ዓ.ም የእርግዝና ክትትሌን እንደወትሮ ለማድረግ ከባለቤቴ ጋር ልጆቻችንን ት/ቤት አስገብተን “ሉዓላዊ” የሚለውን ዝማሬ እያዳመጥን ከመሃተመ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ከጠዋቱ 2:45 ደረስን።
ተራዬ ደርሶ የአልትራሳውንድ ምርመራ ክፍል ገባሁ። ከቆይታ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ይጠይቀኝ ጀመር። ለምሳሌ ልጅ አለሽ? እርግዝና ወቅት የገጠመሽ ለየት ያለ ነገር ነበር? እና መሰል እኔም በአግባቡ መለስኩለት።
ትንሽ ግርታ ከዶክተሩ ፊት ላይ ማንበብ ችያለሁ። ሆንም በጥያቄ ትኩረቱን መረበሽ አልፈለኩም። ግን የእንሽርት ውሃው ከመጠን በእጅጉ መብዛቱን ነገረኝ። አልደነገጥኩም ይህን ከሰማሁ ወር ሆኖኛልና።
በግምት 25-30 ደቂቃ ካየኝ በኋላ ትንሽ ውጪ ጠብቂኝ አለኝ። እኔም መጠበቂያው ክፍል ተቀመጥኩ ከ15 ደቂቃ በኋላም ተጠራሁ ድጋሚ 30 ደቂቃ የፈጀ ምርመራ አደረገልኝ። ለመጨረሻም ጊዜም በሌላ መሳሪያ ደግሞ የመጨረሻ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ ነገረኝ። ከ10 ደቂቃ በኋላ እንደገና ሌላ ለ30 ደቂቃ የፈጀ ምርመራ አደረገልኝና ጨረሰ።
ለመርዶ የቀረበውን ዜና ለመንገር የተጨነቀ ቢመስልም የምርመራው ውጤት የሚያሳየው እትብቱ (የፅንሱ) እርስ በርስ መጠምጠም እንደሚያሳይና ይህ ደግሞ የጽንሱን ዕድገትና ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ እስኪስተካከል የዶክተሮች እጅግ የቀረበ ክትትል ስለሚያስፈልግ በሆስፒታሉ አልጋ ይዤ መተኛቴ ግድ እንደሆነ አስረግጦ ነገሮኝ ወዲያውኑ ወደ አልጋዬ እንድሄድ ተደረገ። ድንጋጤው ይመስለኛል በሞቀ ጸሀይ ብርድ ብርድ ይለኝ ጀምሮ ነበር።
ታዲያ ምን ይደረጋል? በነገር ሁሉ እግዚያብሔር አዋቂ አይደል ፤ ደግሞስ ሉዓላዊም አይደል? ይሁና! አንተ እንዳልክ። ብዬው ወደ ማረፊያዬ ግን እኮ ዕንቁዋ ታብራ ከብሔራዊ ደም ባንክ ጋር በትብብር ላዘጋጀችው (ቅዳሜ ህዳር 25/2014ዓ.ም) የደም ልገሳ ድግስ ሽርጉድ እያልኩ ነበር። አልጋ በያዝኩበት ዕለትም ላከናውናቸው በርካታ ተግባራትን አቅጄ ሰዎችን ቀጥሬ የነበረ ቢሆንም አልተሳካልኝም። ማን ካሰበበት ዋለ??
ይህ የሆስፒታል ቆይታ እንደቀልድ ከህዳር 21-30/2014ዓ.ም ድረስ ቀጠለ የልጄን እንቅስቃሴ መስማት የየዕለት ዋና ተግባሬ ነበር። ስትጠፋብኝ ስጨነቅ ስትንቀሳቀስ ስደሰት ብቻ በአጭሩ የስሜት ህዋሶቼ በሙሉ በሚባል ደረጃ ልጄና ልጄ ላይ ብቻ አተኮሩ።
ሐሙስ ህዳር 30/2014ዓ.ም ፣ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በሰላም ተጠናቀቀ የልጄን አስር እንቅስቃሴ አድምጬ ከተለመደው መመዝገቢያ ላይ በደስታ ስመዘግብ ውያለኋ ከዚህ በላይ ደስታ ምን አለ? ግን ምን ያደርጋል ከቀኑ10:37 አካባቢ የቀኑን ውሎ ፉርሽ የሚያደርግ ነገር ተከሰተ። ውሎ ተቀየረ። ምን ውሎ ብቻ ብዙ ነገሮች ተቀየሩ።
ሩትዬ
አዎ የናፈኳት ፣ ለ8 ወራት የተሸከምኳት፣ ህይወቴን ስሜቴን ስትጋራኝ የነበረች ፣ ላቅፋት የናፈኳት ሩትዬ ከሆዴ ሳለች ጠፍታለች። ከውስጤ ሆና ከእኔ እርቃለች። ያለች መስሎኝ ተለይታኛለች‼
እንዴ ቆይ ስትንቀሳቀስ ነው እኮ የዋለችው እንዴት ሆነ? በቃ ሆነ። ዶ/ሮቹ ሲተጉ የነበረው ትጋት ውሃ በላው። የምድር ጥበብ እጅ ሰጠ ፤ መርዶዬን ሰምቼ ለ35 ደቂቃ ያህል ብቻዬን አንድ ጥግ ተቀምጬ አምርሬ ሌላ ሰው የማይሰማውን የምጥ ለቅሶ አለቀስኩ። አምላኬን በጥያቄ ሞገትኩ።
በመሃልም ጌታ ሆይ አሁንም ዕድል አለ ፤ አንተ እኮ የህይወት አምላክ ነህ ፤ ከሳይንስ በላይ ነህ ፤ ከሞትም በላይ ነህ ፤ አልኩ በየመሃሉ ዳግም እንቅስቃሴዋን ለመስማት እየታገልኩም እየተመኘሁም። ግና እንቅስቃሴ የለም። ሰማይ ዝም አለ!!
ባለቤቴ ደረሰ እሱን ሳገኝ ያኔ ከደረቱ ተለጥፌ እስኪበቃኝ ድምጼን አሰምቼ ተንሰቀሰኩ። እሱም እቅፍ አድርጎ እስኪወጣልኝ ጠበቀኝ።
መኝታ ክፍሌ ልታየኝ የመጣችው እናቴን አስቤ ለጊዜው ለቅሶዬን አቋረጥኩት። እሷ ጋር ስደርስ ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰልና በሰላም ወደ ቤት እንድትሄድ የማድረግ ከባድ የቤት ስራ ነበረብኝ። እናም ፊቴን ታጥቤ ሃዘኔን ዋጥ አድርጌ ውዷ እናቴን እንደምንም በሰላም ሸኘኋት። እንደወጣች ለቅሶዬና በቅጡ ያላወኩትን የተዘበራረቀ ስሜቴ መልሶ ከበበኝ።
እጅግ ከባድ ሃዘን ልቤን ሁለንተናዬን ሞላው ያለማቋረጥ የፊቴን እየለበለበ የሚወርደው እንባዬን ልገድበው አልቻልኩም። ብዙ ትዝታዎች፣ ናፍቆት ፣ እነዚያ የጭንቅ ቀንና ለሊቶች ያለ ፍሬ መቅረታቸው ፣ የእግዚያብሔር በዚህ ሰዓት አዳኝ ሆኖ አለመገለጡ ፣ ከሚያስለቅሱኝ ነገሮች ጥቂቶቹ ነበሩ።
ብቻ ህዳር 30/2014ዓ.ም ዕለተ ሀሙስ ምሽት ከሌላው ቀን ይልቅ ድቅድቅ ነበረ። የመከራ ፓኬጁ ሩት ከመጥፋቷ ቢጀመርም ቀጥለው የነበሩት ሶስት ቀናት እጅግ የከፉና የውጥረት ጊዜያት ነበሩ። ከማህጸን ማለስለስ ፕሮቶኮል አንስቶ እስከ የምጡ ስቃይ ጫፍ ድረስ በየመሃሉ ብቅ እያለ እዬዬ ሲያስብለኝ የነበረው “ይሄ ሁሉ ጭንቅ ለማላቅፈው ልጅ ነው” የሚለው ነፍስ የሚሰነጥቅ እውነታ ጋር ለሶስት ቀናት መታገል ሞትን አቅልዬ እንዳስብ አስገድዶኝ ነበር። ለካ ሰው ራሱን የሚያጠፋው ከሞት የገዘፈ ነገር ሲገጥመው ኖሯል‼
ግን ደግሞ ይህን እኔ ምን ላደርገው ይቻለኛል? ላስተካክለው የምችለው በእኔ እጅ ያለ ነገር አይደለም!! ልለውጠው አልችልም! ይህን ማድረግ የሚችል አቅምም ፣ ሃይልም ፣ ችሎታም የለኝም!! ግን የሰው ውስንነት ምን ያህል እንደሆን ገባኝ። ለካ ምንም ማድረግ የማንችላቸው ነገሮች አሉ። ከእኛ ችሎታ በላይ እጅግ የበረቱ ናቸውና። ያለ አንዳች ፍርሃት ወደ እኛ መጥተው “እጅ ወደ ላይ!” የሚሉን ፣ የማንታገላቸው ፣ አምርረን ልንታገላቸው ብንነሳ እንኳ በታገልናቸው መጠን ማሳመማቸው ዘልቆ የሚሰማን ከአቅማችን በላይ የሆኑ ነገሮች አሉ። የሚያዋጣው እጅ ወደላይ ብቻ ፤ መስማማት ብቻ!!!
ሀሙስ ማታ የተጀመረው የምጥ ነገር እስከ ቅዳሜ እኩለ ለሊት ዘለቀ። በመጨረሻም ከአምላኬ የተዘጋጀልኝ ዶ/ር ግርማ በሚያስደንቅ እንክብካቤ ጋር ያ አሰጨናቂ የምጥ ጊዜን በ15 ደቂቃ የማዋለድ ስርዓት ደመደመው። (በዚህ የጭንቅ ጉዞ ቀሎልኝ ያለፍኩት የመውለጃ ጊዜዬ መሆኑ ሳስብ ተውከኝ ያልኩት አምላኬ ከእኔ ጋር ሳያቋርጥ አብሮኝ እንደነበር ብርቱ ማስረጃ ነው።) ይሁንና ‘እንደ እናት ከማህጸኔ ስትወጣ ድምጿን ለመስማት መናፈቄ ፣ ለማቀፍ ፣ ከደረቴ ላስጠጋት መጓጓቴ አልቀረም። ግን በቃ አልሆነልኝም¡
ምንም እንኳን ሞኝነት ቢመስልም እስከዛን ሰዓት ድረስ የእግዚያብሔርን ጣልቃ ገብነት እጠባበቅ ነበር። ግን አልሆነም ፤ ይልቁን ዓይኔ እያየ ነርሷ እንደ ቀልድ በጨርቅ ጠቅልላት ይዛት ሄደች። ልቤ ተከተላት ፤ ግና አልደረስኩባትም በዚህ ሁሉ ውስጥ ታሪክን የሚለውጠው ፤ ነገር ሲያበቃ የሚጀምረው ሰማይ ዝም አለ!!
ቢሆንም ‘ለሞተም ፤ እንደማያቅፉት ለሚያውቁትም ጽንስ ይማጣል ፤ ያውም በእጥፍ ስቃይ። በመጨረሻም ህይወት የሌላትን በድን ልጄን ወለድኳት።
“ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው!”
የተባለው ፈሊጣዊ አባል በማይሰራ ጊዜስ?
ምጤን ስቃዬን ምን አንስቼ ልርሳው? መርሳት የለም! እውነታውን ተግቶ ከመጨለጥ ውጪ ምርጫ የለም! አከተመ!!
ደሞ ሌላ እህህህህ ፤ የሚጠባው የሌለ በወተት የተሞላ ያጋተ ጡት ፤ በወጠረኝ መጠን ናፍቆቴን ሲጨምረው ፤ ሌላ ሃዘንን ጨመረብኝ። ያዋለደኝ ዶ/ር ግርማ ሂርጴሳ በጡት ማስያዣ እንድይዘውና ፓናዶል እንድጠቀም ባይነግረኝ ስቃዩ ባንገላታኝ ሌላ ህመም በሆነኝ ነበር። ግን ተረፍኩ። ዶ/ርዬ አመሰግንሃለሁ።
በዚህ ሁሉ “ዕንባ” የውስጥን ትኩሳት በብዙ ቢያበርድም ከዚያ በላይ ለበዛው የውስጥ ስብራት ግን ሙሉ መፍትሄ አይሆንም። ከእኛ የገዘፈ ችግር የገጠማቸውን ሰዎች ተሞክሮም ማሰብና ከእኛ ጋር በማነጻጸር መጽናናት አይሞከርም። የብዙ ሰዎች ልዝብና አስተዛዛኝ ቃሎችም እምብዛም አይጠቅሙም። በእኔ እምነት ያለው መፍትሄው አንድ ነው እርሱም በእሳቱ ሰዓት ላይ የሚረዳን አይደለም ሆኖም ቀን በቀናት ላይ ሲደራረብ ወደራሳችን መለስ ስንል ይሄን ለእኔ መፍትሄ መድሃኒት የሆነልኝን እውነት ካሰብን በርግጥ ይረዳናል የሚል እምነት አለኝ።
አዎ የእግዚያብሔርን ታማኝነት ፣ አባትነት ፣ መልካምነትን ፣ በደንብ ማስታወስ!! ከሱ ቀጥሎ እሱ ለእኛ ሁልጊዜም ቢሆን የተሻለውን እና የሚረባንን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን ማመን። ይህ ለእኔ ፈውስን ያመጣልኝ ስሜቴን ያከመልኝ ሃዘኔን የገፈፈልኝ እውነት ነው። ልጄን ባጣኋት በሁለተኛው ሳምንት ልቤ ተጽናንቶ አምላኬን ከልቤ ማመስገን ጀምሬያለሁ።
ለጠያቂዎቼም በደስታ እግዚያብሔር ለእኔና ለቤተሰቤ የተሻለውን አድርጓል ብዬ እመሰክራለሁ። ይሄም ብቻ አይደለም ነፍሴ በሰላም አርፋለች እንባዬም ከአይኔ ደርቋል።እግዚያብሔር ለልጆቹ ሁልጊዜ የተሻለውን ያደርጋል!
እየሩሳሌምን ለማግኘት ፣ እርዳታ ለማግኘት ፣ አላማዋን ለማገዝ ፣ እንዲሁ ከእንቁዋ ታብራ ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት በሚከተሉት አድራሻዎች እና በማህበራዊ ሚዲያ ልታገኙአት ትችላላችሁ።
👉🏽 ቢሮ : ቄራ ቶታል አካባቢ ኪዳነ ምህረቱ ህንጻ 6ኛ ፎቆ ቢሮ ቁጥር 608
👉🏽 ስልክ : +251 97 007 0404
👉🏽 ኢሜል (Email) eyerunegash4@gmail.com
👉🏽 ፌስ ቡክ (Facebook) : https://www.facebook.com/Enquwa?mibextid=LQQJ4d
👉🏽 ኢንስታግራም (Instagram) : https://instagram.com/enquwa_tabra?igshid=YmMyMTA2M2Y=
Leave a Reply