ሁሌም እንደምለው እና ዛሬም በ አንክሮ የምደግመው ነገር ቢኖር ሁላችንም ወላድ እናቶች የወሊድ ታሪኮቻችንን ወደ ፊት በማምጣት ልንነጋገርባቸው ፣ ልንማማርባቸው እንዲሁም በቃል ያለ ይረሳል በፅሁፍ ያለ ይወረሳል እንዲሉ ወረቀትን ከብዕር አገናኝተን ልንሰንዳቸው ይገባል። ለዚህም ሲባል ዛሬ የእናት ጊፍቲን ተፈጥሮአዊ የወሊድ ታሪክ ይዤላችሁ ስቀርብ በታላቅ ሀሴት እና ክብር ነው። ጊፋቲንም ታሪክሽን ስላጋራሽን ምስጋናችን የላቀ ነው እንላለን፤ ይልመድብሽ።
አንባቢዎች መቼም የወሊድ ታሪኳን አሁን የምናነብላት ጊፋቲ ለመሆኑ ማን ነች ብላችሁ ሳትጠይቁ አትቀሩም። ላስተዋውቃችሁ።
ጊፍቲ በሙያዋ ደግሞ የግራፊክስ ዲዛይነር ነች። እንደውም የተወሰኑ ስራዎቿን በዚህ ሊንክበመታገዝ ልትመለከቱ ትችላላችሁ። ጊፍቲ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ስትሆን በአሁን ጊዜ ላይ ሙሉ ጊዜዋን በቤት ውስጥ በመሆን ልጆችዋን በማሳደግ ላይ ትገኛለች። የምትኖረው በአሜሪካ ዲሲ-ሜሪላንድ-ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ ሲሆን ሁለት ቋንቋ ደርበው መናገር የሚችሉትን ልጆቿን ስታሳድግ መደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ላይ ሙጭጭ ያላለው የ "ሞንቴሰሪን" (Montessori) የልጆች መር የትምህርት አሰጣጥ ልምምድ በመከተል ነው።
ጊፍቲ ስለ እናትነት ጉዞዋ፣ አጋዥ ናቸው ብላ ስለምታምንባቸው የልጆች አስተዳደግ ክህሎቶች ፣ የትምህርት ማስተማር ስልቶች እንዲሁም የምግቦችን አዘገጃጀት በኢንስታግራም/Instagram/ ላይ ሳትታክት ለ ተከታዮቿ የምታጋራ ብርቱ ሴት ነች። እስከ አሁን ድረስ አካውንቷን ካልጎበኛችሁ በዚህ ሊንክ ማግኘት ትችላላችሁ።
ምጥን ያለ ፍርሃት
በጊፍቲ ባዩ እንደተፃፈው
እርግዝናዬ
እውነት ለመናገር የመጀመሪያዎቹ የእርግዝናዬ ሳምንታት የጤንነት አየር ከእኔ ርቆ የነፈሰበት ወቅት ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በጣም ይደክመኝ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው በመተኛት ነበር።
ሆኖም ሶስተኛ ወሬን አገባድጄ ወደ አራተኛው ስንደረደር ርቆኝ የነበረው ጤንነቴ ቀስ በቀስ ተመለሰልኝ። እንደውም የመጀመሪያ እርግዝናዬን በሚያስንቅ መልኩ ይኸኛው እርግዝናዬ እጅግ ሰላማዊ ነበር። በተለይ ወደ መጨረሻ።
ሁሌም በየሳምንቱ ካይሮፕራክተሬ ጋር እሄድ ጀመር ፤ ይሄ ደግሞ ሰውነቴ እንዲቀለኝ በጣም ረድቶኛል። ምንም እንኳን ሁሉን ነገር ለማየት እና ለመሞከር ድክ ድክ የሚለው የበኩር ልጄ ከጎኔ ቢሆንም ለእርግዝናዬ ብዬ የቆጠብኩትን ኃይል እና ብርታት አልነጠቀኝም። እኔም ብሆን ሰውነቴን ከማዳመጥ እና በተገኘው ጊዜ ሁሉ ጎኔን ከማሳረፍ ከቶ አልቦዘንኩም ነበር።
ወሬ እየገፋ በመጣ ጊዜ ሌላው ይፈትነኝ የነበረው ነገር እንቅልፍ በምተኛበት ጊዜ ትንፋሽ የሚያጥረኝ ነገር ነበር። ስንትም ሰዓት ብተኛ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን እንደ አውራ ዶሮ ባንኜ መነሳት የእለት ተእለት ግብሬ መሆን ጀመረ። ከዚያን ወዲህ እንዲሁ ኮከብ ስቆጥር ሌሊቱ ይነጋል። ይሄንን የተዛባ የእንቅልፍ ዑደቴን ለመካስ ቀን በአገኘሁት ጊዜ ሁሉ ለመተኛት እሞክራለሁ።
የመጨረሻዎቹ የእርግዝናወራት እና የወሊድ ምጥ
በመጀመሪያው እርግዝናዬ ወቅት ምጥ በራሱ ጊዜ ሳይሆን በምጥ መርፌ አጋዥነት ስለነበር የመጣው በዚህኛው እርግዝናዬ ሰውነቴ እንዴት እንደሚሆን የማውቅበት ምንም አይነት መንገድ አልነበረም ተፈጥሮን ከመጠባበቅ ውጪ። ግን ደግሞ ውስጤ ሰላሳ ዘጠነኛውን ሳምንት ስጨርስ ልጄን እንደምታቀፈው ይነግረኝ ነበር።
ይሁንና ያ በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ሰላሳ ዘጠነኛ ሳምንት ደርሶ አየሁት እርሱ ግን መልሶ ላያየኝ እንደ ከ እሱ ቀደሞቹ ሳምንታት ሁሉ ያለ ምንም የምጥ ስሜት ተራውን ለቀጣዩ ሳምንት አስረክቦ ነጎደ። ይሄ እንዲህ ሲሆን ውስጤ ሀሳብ ይገባው ጀመር ፤ "እንዴት ነው ነገሩ? ምጥ እስከ አርባ ሁለተኛው ሳምንት ድረስ ሊቆይብኝ አስቦ ይሆን....?" እያልኩ እራሴን ብጠይቅም መልሼ ደግሞ ሰውነቴን ማዳመጥ ነው የሚበጀኝ ብዬ እራሴን ማረጋጋት ተያያዝኩኝ።
ከአምስት ቀናት በኋላ በቀጠሮዬ መሰረት አዋላጅ ነርሴ ጋር ለመታየት አመራሁኝ። ግን በውስጤ በዚህኛው እርግዝናዬ ተደጋጋሚ የማህፀን ምርመራ ላለማድረግ ነበር የወሰንኩት። ምክንያቱም የሰውነቴን ለምጥ መዘጋጀት ለማወቅ ብቸኛ መንገድ ይሄ እንዳልሆነ ስለማውቅ ፤ ነገር ግን ደግሞ መልሼ ሳስበው ወሬ ሊገባደድ ሁለት ቀናት ብቻ መቅረቱ ሰውነቴ ምን ያህል ለምጥ እንደተዘጋጀ የማወቅ ጉጉቴን ይበልጥ ጨምረውና ለመታየት ወሰንኩኝ።
እዚያው ከደረስኩኝ በኃላ አዋላጅ ነርሴ ምርመራውን አድርጋ ስታበቃ የማህፀኔ በር ጫፍ አንድ ሳንቲ ሜትር ብቻ የተከፈተ መሆኑን ገለፀችልኝ። ይህም ማለት አለች አስከትላ ምጥ በዚህ በያዝነው ሳምንት የመምጣት እድሉ እጅግ የመነመነ ስለሆነ በእግሬ እንቅሰቃሴ እንዳደርግ አበረታታኝ ተለያየን።
የወሊድ ቀን
በቀጠሮየ ማግስት፤ ቀኑ እንደ ሌሎቹ ቀናት በቀላሉ አልገፋም ያለኝ ገና ከማለዳው ነበር። ተመላልሼ አልጋዬ ላይ በመውጣት ለመተኛት ሞከርኩኝ። ሰዓቱ ገፋ ሲልም ከእናቴ ጋር በ መሆን ቡና ለመጠጣት በዛውም እግሬን ለማፍታታት ከቤቴ ወጣሁኝ። ለ 45 ደቂቃዎች ያህል ከተራመድኩኝ በኋላ በሆዴ ያለው ፅንስ ወደ ታች ይገፋኝ ጀመር ግን ያን ያህል የጠነከረ ህመም አልነበረም።
ቀሪው የዕለቱ ከሰዓት ግን ህመም አልባ ሆኖ ነበር ያለፈው። ራቴን በሰላም በልቼ ስመለስ የልጄን በማህፀኔ ውስጥ ያለውን አቀማመጥ ለማቃናት የሚረዳኝን እንቅስቃሴ (miles circuit exercises) መስራት ጀመርኩኝ። እንቅስቃሴውን እየሰራሁኝ እራሴን ከምጡ ሀሳብ ለማዘናጋት ፊልም ከፍቼ እያየሁኝ ስፖርቱን ቀጠልኩኝ።
ከ ምሽቱ 5:30 ግድም ሲሆን ትንሽ በአይነቱ ለየት የሚል የቁርጠት ስሜት (contraction) ይሰማኝ ጀመር። እኔ ግን ብዙም ቦታ ልሰጠው ስላልፈለግኩኝ ፊልሜን እያየሁ እንቅስቃሴዬን መቀጠሉን መረጥኩኝ። እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ስሜቱ እየበረታብኝ መጣ።
ከ ሰላሳ ደቂቃ በኃላ ለባለቤቴ ሄጄ እጅግ በተረጋጋ ስሜት እና መንፈስ "ምጥ እየጀመረኝ ነው መሰለኝ..." በማለት ነገርኩት ምንም የተሸበርኩኝ ሳልመስል። ቀጥዬም የተወሰነ ጉልበት እንኳን ከሰጠኝ በማለት ወደ መኝታዬ ሄጄ ለማረፍ ሞከርኩኝ። ግን አልተሳካልኝም ቁርጠቱ እየበረታብኝ ሲመጣ ምቾቴን ስለነሳኝ ዳግም ከአልጋዬ ተነሳሁኝ።
ባኞ ቤት ውስጥ ሳለሁ መፀለዩን መዘምር እና መወዛወዙን ከምጥ ጋር ቀጠልኩኝ። ትንሽ እንደቆየሁ እየተሰማኝ ያለው ስሜት አውነተኛ ምጥ መሆኑን ለመለየት ስል ደቂቃ ይዤ ቁርጠቱን (contractions) መቁጠር ጀመርኩኝ። ውጤቱም እጅግ አስገረመኝ ፤ ለካስ በየሁለት ደቂቃው ቢያንስ ለሃምሳ ሴኮንዶች ያህል የሚቆይ ቁርጠት ከጀመረኝ ሰነባብቷል። ቶሎ ብለን ለአዋላጅ ነርሳችን ጊዜ ሳናጠፍ መደወል እንዳለብን ተስማማን።
ቁርጠቱ በሃይል ወደ ታች ይገፋኝ እንደጀመረ ሳስተውል “እውነተኛው” ምጥ ሲመጣ ምን ልሆን ነው ብዬ ሃሳብ ገባኝ።
ባኞ ቤት ውስጥ ሳለሁ መፀለዩን መዘምር እና መወዛወዙን ከምጥ ጋር ቀጠልኩኝ። ትንሽ እንደቆየሁ እየተሰማኝ ያለው ስሜት አውነተኛ ምጥ መሆኑን ለመለየት ስል ደቂቃ ይዤ ቁርጠቱን (contractions) መቁጠር ጀመርኩኝ። ውጤቱም እጅግ አስገረመኝ ፤ ለካስ በየሁለት ደቂቃው ቢያንስ ለሃምሳ ሴኮንዶች ያህል የሚቆይ ቁርጠት ከጀመረኝ ሰነባብቷል። ከባኞ ቤት ስወጣ ቁርጠቱ በሃይል ወደ ታች ይገፋኝ እንደጀመረ ሳስተውል ቶሎ ብለን ለአዋላጅ ነርሳችን ጊዜ ሳናጠፍ መደወል እንዳለብን ተስማማን።
የወሊድ እቅዴ የነበረው የተቻለውን ያህል በቤቴ አምጬ ቀሪውን ደግሞ በወሊድ ማዕከሉ በዉሃ ውስጥ ሳለሁ መገላገል ነበር።
ከሌሊቱ 8:00 ሰዓት ላይ ብርቱ የሆነ ምጥ እኔን እያስማጠኝ ባለበት ወቅት ባለቤቴ ከአዋላጅ ነርሴ ጋር በስልክ እያወራ ነበር። እሷም የድምፄን ሃይል በስልክ አሻግራ ስትሰማ ሁለተኛው የምጥ ደረጃ ውስጥ ብትሆን ነው እንዲህ የበረታባት በማለት ግምቷን ከነገረችው በኃላ አሁኑኑ ወደ ወሊድ ማዕከሉ በፍጥነት እንድንሄድ ነገረችን። ባለቤቴ ወዲያውኑ መሰነዳዳት ጀመረ። እኔም ከምጥ ጋር እየታገልኩኝ ልብሴን ከቀያየርኩኝ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ማዕከሉ አቀናን።
ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ማለትም ከሌሊቱ 8:30 ግድም በ በማዋለጃ ማዕከሉ, ከተገኘሁኝ በኋላ መጀመሪያ አልጋውን በቁሜ ተደግፌ የተወሰነ ያህል ካማጥኩኝ በኋላ አልጋው ላይ በመውጣት ደግሞ ቀሪውን ሃይሌን በማሰባሰብ ማማጡን ቀጠልኩበት።
ወደ አንድ ሰዓት በዚሁ ሁኔታ ከቆየሁኝ በኋላ ልጄ ከእነ ሽርት ውሃው ከረጢት ሳይፈነዳ ከሌሊቱ 10:19 በሰላም ተገላገልኩኝ። ወዲየውኑ በእግሩ የሽርት ውሃውን ከረጢት ካፈነዳው በኋላ አዋላጅ ነርሴ ልጄን በመያዝ ሙቀት እንዲያገኝ ከደረቴ ላይ አኖረችልኝ።
ሁሉም ነገር በቶሎ ቶሎ ስለተከሰተ እንደ ፍላጎቴ በሙቅ ውሃ ውስጥ ሆኜ ልጄን ባልገላገለውም ፤ እንዲሁም የወሊድ አጋዤን (doula) ለማግኘት ባያደርሰኝም ባለቤቴ ግን በሁሉም ነገር ከጎኔ በመሆን በጣም በጉልህ አበርትቶኛል። ይሄም ደግሞ አብረን ለወሊድ እና ምጥ የሚያግዙን ትምህርቶችን (birth course) መውሰዳችን ነገሮችን ሁሉ እንዳቀለለን አምናለሁ።
በመጨረሻም ህፃን ኢባን በአርባኛው የእርግዝናዬ ሳምንት ማገባደጃ 8 ፖውንድ ክብደት ከ20 ኢንች ቁመት በመያዝ በፍፁም ጤንነት ወደዚህች አለም ተቀላቀለ።
መለስ ብዬ ሳየው ይሄኛው እርግዝናዬ በእውነቱ ነገሮች ሁሉ ከጠበቅሁት በላይ ሆኖ ያገኘሁበት ሲሆን ፤ እኛ ሴቶች ለዚህ ተፈጥሯዊ ታምራት መታጨታችን እና መወጣታችንን ሁሌም ባሰብኩት ጊዜ ታላቅ አግራሞት ጭሮብኝ የሚያልፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
በዚህ እርግዝናዬ አምላኬን ፦
የጠየቅኩት፦
- ጤናማ እርግዝና እና ልጅ
- ሁሉን የምወጣበትን ሃይል እና ጉልበት
- ወሬ ሳይገፋ በሰላም እንድገላገል
- ምጤ እንዳይበረታብኝ እና እንዳይረዝምብኝ
- ሽርት ውሃዬ ቀድሞ እንዳይፈስ
- ወደ ሆስፒታል ሪፈር ሳልባል በ ሰላም እንድገላገል
- ቶሎ እንዳገግም ሁሉ ጠይቄ ሁሉንም እንደምኞቴ የፈፀመልኝ እርግዝናዬ ስለሆነ ለ እኔ ልዩ ነው።
መውለድ ውብ ስጦታ ነው። አንዴ ስነ ፍጥረታችንን ልብ ብለን ብናየው ይሄንን ውብ ስጦታን በሰላም እንድንወጣው ፈጣሪ ሁሉንም አሟልቶ የፈጠረን የእጁ ውብ ስራዎች መሆናችንን አስተውያለሁ።
Rahel
Ohoo my God ! interesting birth stories , congratulations! Am so proud of u . You are the best Mom . Natural birth is the best . Thanks God ! I get power from you ! Me and my friend we have plane to do naturally but we have fear I hope next year with out fear we gonna decide to get pregnant please contact me. I live in California. You gonna explain me more how I can get Midwife . Am new for this group. I love Holistic Mom’s
Thank you son much Blessed family .
Congratulations!!!! Beautiful baby .
ሐና ኃይሌ
Thank you for kind words Rahel. And it is nice you have interest for natural birth. Will definitely contact you and help in any way possible.