በዚህኛው የብዕር ክታብ አንዲት ባለ አስገራሚ እና አነቃቂ ህይወት ባለቤት የሆነች ማማ ስቴፋኒ የወሊድ ታሪኳን ታካፍለናለች። በመጀመሪያ ማን እንደሆነች በጥቂቱ ላስተዋውቃችሁ።
ስቴፋኒ የአንድ ወንድ ልጅ እናት ነች። ጀርመናዊት የስነ ህይወት ተመራማሪ እንዲሁም የብዝሃ ህይወት ጠባቂ ነች። ይሄ ከተፈጥሮ ጋር ያላት የጠበቀ ቁርኝት ገና በለጋ እድሜዋ በታንዛኒያ ውስጥ የበጎ ፍቃድ ስራ እንድትሰራ በር ከፍቶላታል። በደቡብ ዛንዚባር የማፊያ ደሴት ምርምር ካምፕ ውስጥ ሳለች የአሁኑን ትዳር አጋሯን ሶኮይኒ ጋር ልትገናኝ በቃች።
ባለቤቷ ሶኮይኒ ማሳይ ነው። ማሳይ (Massai) በታንዛኒያ የሚገኝ ጥንታዊ የጎሳ ማህበረሰብ ነው። ስቴፋኒ ከሰፊው የባለቤቷ ቤተሰቡ ጋር ተቀላቅላ ቦማ በሚባለው ባህላዊው የማሳይ ቤት በመኖር እና ልጇቸውን በማሳድግ ላይ ትገኛለች።
ምንም እንኳን በምዕራባዊ ባህል ተቃኝታ ያደገች ቢሆንም ስቴፋኒ ከባለቤቷ ወገኖች የህይወት ዘይቤ ጋር ተመሳስላ ከአስር አመታት በላይ እየኖረች ትገኛለች። ይሄን ስታደርግ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ እንዳልነበረላት ለመገመት አይቸግርም። በምጥ እና በወሊዷ ወቅት የገጠማትም ፈተና አንዱ ሲሆን ይበልጡኑ ደግሞ ቀጥሎ የቀረበውን የወሊድ ታሪኳን ስታነቡ የምታገኙት ይሆናል።
በተጨማሪም ሌሎች ታሪኮችን ለማግኘት የኢንስታግራም ገጿን መጎብኘት ትችላላችሁ። በጀርመንኛ ቋንቋ የፃፈችውንም መፅሀፍ ማግኘት ትችላላችሁ።
አሁን ወደ ወሊድ ታሪኳ እንግባ።
በስቴፋኒን ፉክስ እንደተፃፈው
እናት መሆን በታንዛንያ ማሳያዎች መካከል
በተፈጥሮ መንገድ መወለድ ሁልጊዜም ቢሆን ፅኑ ህልሜ እና ምኞቴ ነበር። ሁላችንም እንመኛለን፤ አይደል?
ምንም እንኳን ተፈጥሯዊ ወሊድ የልቤ መሻት ቢሆንም የገዛ ሰውነቴን ግን ማመን ይሳነኝ ጀመር። ምክንያቱም በባህላዊ የማሳይ አዋላጅ ነርሶች ታግዤ በሰላም መኖሪያ ቤቴ ውስጥ መገላገል ስችል በዳሬ-ሰላም ሆስፒታሎች ውስጥ መገላገልን የምመኘው ሌላ ምንም ምክንያት ኖሮኝ አይመስለኝም ፤ የገዛ ሰውነቴን አለማመን እንጂ።
ልጄ በተወለደበት ጊዜ ከባለቤቴ ትውልድ ሰዎች (ከማሳይ ህዝቦች) ጋር አብሬ መኖር ከጀመርኩኝ አራት አመታት አልፈው ነበር ። በእነዚህ አመታት አያሌ የሚባሉ ሴቶች በራሳቸው መኖሪያ ቤት በሴት ዘመዶቻቸው ብሎም በልምድ አዋላጆች አማካኝነት ታግዘው በሰላም ሲገላገሉ ለመታዘብ ችያለሁ።
ይሄንንም ሲያደርጉ እንዴት ሰላማዊ እና ቀላል እንደሆነላቸውም ጭምር መመልከት ችያለሁ። ነገር ግን ያም ሆኖ እኔም ብሞክረው ሁኔታዎች እንደ እነርሱ በሰላም ያልፍልኛል ብሎ ማሰቡ አልሆንልሽ አለኝ። በጊዜው የሃያ ዘጠኝ አመት ወጣት ነበርኩኝ።
አሁን ላይ መለስ ብዬ ስለዚያ ወቅት በማስብበት ጊዜ አዕምሮዬ ላይ የነበረው የሀሳብ ፍጭትን በመጠኑም ቢሆን ምክንያቱን ለመረዳት የቻልኩኝ ይመስለኛል። ይሄም በአንድ በኩል በማሳይ ሴቶች ላይ ያለኝን እምነት አጠንክሬ በእነሱ አጋዥነት በሰላም መገላገልን ብፈልግም በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራባዊያን አስተሳሰብ የተቀረፅኩ መሆኔ ደግሞ የወሊድን ምንአልባታዊ አደገኝነት ቸል ብዬ የቤት ውስጥን ወሊድን መምረጥ ፈታኝ አድርጎብኛል።
ያኒክ ልጄ ሰባት አመት ሊሞላው ነው። እኔ ግን አሁንም እሱን ልወልድ ስል እና ከወለድኩም በኅላ የገጠሙኝን መከራዎች ልክ ትላንት እንደተከሰቱ ያህል ከውስጤ ሊጠፉ አልቻሉም። እሱ የመጀመሪያዬም የመጨረሻዬም ነው ለጊዜው። ለነገሩ ከአሁን በኋላ ሌላ ልጅ የመውለድ ሀሳቡም እቅዱም የለኝም። ምክንያትሽ ምን ይሆን ካላችሁኝ እጅጉን ፍርሃት ስለሚያረበርበኝ ነው። ድጋሚ ራሴን ባጣስ፣ ድጋሚ ያን ቀፋፊ ድባቴ ተመልሶ ቢመጣብኝስ ፣ ድጋሚ ደስታ ከእኔ ርቃ ብትሸሸኝስ እያልኩ እሰጋለሁ።
ከባለቤቴ ሶኮይኒ ጋር የማሳይን መንደር ለቀን ወደ ታላቋ ዳሬ-ሰላም ከተማ ለማቅናት የወሰንነው ወሬ ከመግባቱ ሁለት ሳምንታት አስቀድመን ነበር። እዚያህ ደርሰን ልጄን ከሆስፒታል ሆኜ መገላገል ነበር ምኞቴ። በእኔ ቤት የተሻለውን ምርጫ መምረጤ ነበር ።
በወርሃ የካቲት በአስራ ሶስተኛው ቀን እ.ኤ አቆጣጠር 2016 ዓ.ም መሆኑ ነው ማለዳ ላይ የቁርጠት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ከሁለት ወር በፊት የበኩር ልጇን የወለደች ጓደኛዬ የነገረችኝን አስታወስኩኝ። ‘’የምጥ ህመም ማለት ልክ ወር አበባ ሊመጣ ሲል የሚሰማን የህመም አይነት ሲሆን ይሄኛው ልዩነቱ እጅግ ብርቱ መሆኑ ነው። ‘’ ያለችኝን አስታወስኩኝ።
የዛውኑ ቀን ማታ ላይ ምጡ እጅግ በረታብኝ እና ወደ እኩለ ሌሊት ላይ ሆስፒታል ለመግባት በቃሁኝ።
ከዚያም ወዲያ አንድ ለአይኔ አዲስ የሆነ ወንድ ነርስ ወደ እኔ ቀርቦ የማህፀን ምርመራ ማድረግ ጀመረ። እኔ ግን እየሆነ ባለው ነገር ምንም አይነት ምቾት ሊሰማኝ አልቻለም። ሌላው ቢቀር ዶክተሬ ወይም ደግሞ ሌላ ሴት ነርስ ምርመራውን ብታደረግልኝ ብዬ መመኘቴ ግን አልቀረም።
ሆስፒታሉ ቀዝቃዛ ቢሆንም እጅግ ፅዱ እና ደመቅ ባሉ መብራቶች የተዋበ ነው። ቀጥሎም ክፍሌን ከጠቆሙኝ በኋላ በመተላለፊያው ማብቂያ ላይ ባለው ደረጃ ላይ ከባለቤቴ ጋር እንድንቀሳቀስ ተነገረኝ። ከዚያም ወዲያ እኔ እና ባለቤቴ እንዲሁም እንቅልፍ ከነሳኝ ህመሜ ጋር ሆነን ምሽቱን ተያያዝነው።
እጅግ በሚያበሽቅ ሁኔታ ራሴ እና ሰውነቴ ላይ ትኩረቴን ከማድረግ ይልቅ ሃሳቤ በባለቤቴ ላይ ፣ በየመሃሉ እየመጡ በሚያዩኝ ፀጉረ ልውጥ ነርሶች ፣ እና ባልተወለደው ልጄ ዙሪያ ይከፋፈልብኝ ጀመር።
እየሆነ ያለው ነገር ለሰውነቴም ሆነ ለአዕምሮዬ ስቃይ ሆኖ ይሰማኝ ጀመር። ፈፅሞ ደስተኛ አልነበርኩም። ሰውነቴም ቢሆን በምንም አይነት ዘና ሊል አልቻለም ይልቁንም በእጅጉ ተሸብሬያለሁ። እንዲህ ከሆነ ወሊድ ፤ እንዴት ይሆን ልጄ በተፈጥሯዊ መንገድ ሊወለድ የሚችለው እያልኩኝ በውስጤ መብከንከን ጀምሬያለሁ።
በቀጣዩ ቀን ከማለዳው ሶስት ሰዐት ግድም የማህፀን በሬ ወደ ሰባት ሳንቲ ሜትር ያህል ስለተከፈተ ወደ ማዋለጃ ክፍል ተወሰድኩኝ። ከአምስት ሰዓታት ቆይታ በኋላ በሚፈለገው መጠን የማህፀን በሬ ስላልተከፈተ አዋላጅ ነርሴ ከዶክተር ጋር ለመማከር በቁ። በንግግራቸው መሃል በቀዶ ጥገና ማዋለድ (C-section) የሚል ቃል ከአፋቸው እንደወጣ አዕምሮዬ "አዎ ባይሆን እሱ ስሜት ይሰጣል።" እያለ ለራሴ በውስጤ ማስተጋባት ጀመርኩኝ። እናቴም ቢሆን ሁለት ጊዜ ያህል ኦፕሬሽን አድርጋለች ፤ ለእኔም ይሄ ይመስለኛል ዕጣ ፈንታዬ እያልኩ በውስጤ ማሰላሰሉን ተያያዝኩት።
አሁንም መልሼ በሃይል መግፋቴን ስቀጥል አዋላጅ ነርሴ እንዳቆም ነገረኝ። ምክንያቱም በበቂ ሁኔታ የማህፀን በሬ እየከፈተ ስላልሆነ ከዚህ በላይ መግፋቱ እንደማይጠቅመኝ ነገረችኝ። በቂ እንቅልፍ በዐይኔ አለመዞሩ ፣ እህልም አለመቅመሴ ከህመሙ ጋር ታክሎ ሰውነቴን አዝሎታል። የልጄ ልብ ምት መዛባቱን ነግረውኝ ምንአልባትም በ ኦፕሬሽን መገላገል እንዳለብኝ ሲጠቁሙኝ "እሺ!" ለማለት ፈፅሞ አላመነታሁም።
በመቀጠልም ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ተወሰድኩኝ ፤ አፍንጫዬ ላይ የመተንፈሻ ማስክ አድርገውልኝ ኖሯል። ቀጥዬ እራሴን ሳውቅ እጅግ ጥልቅ ከሆነ ሰመመን እንደነቃሁኝ ነበር። የቀዶ ህክምናው ክፍል ለአይኖቼ ደንገዝገዝ ብሏል ፤ ከመስኮቱ ወዲያ ውዱ ባለቤቴን አየሁት። እሱም ተነስቶ ወደ እኔ ሲመጣ አይኖቹ እንባ እንዳቀረሩ አየሁኝ፤ የደስታ እንባ፤ ሰላም ስለነቃሁኝ የፈሰሰ የምስጋና እንባ። በውስጤ ስለ እኔ ሲል እንዲህ ያለ ጭንቀት ውስጥ መግባቱ አሳዘነኝ።
ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ሳመራ ሰዓቱ በግምት ከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር። ኋላ መልሼ ስነቃ ውጪው እጅግ ደንገዝገዝ ብሎ ነበር ፣ ሰዓቱን መልሼ ሳየው ወደ አስራ አንድ ሰዓት ግድም መሆኑን ተረዳሁ። ወዲያውኑ ከሰመመን እንደነቃሁ "ልጄስ? ፤ ልጄ የታል?" በማለት ጠየቅኩኝ።
አንድ ወቅት ሲባል እንደሰማሁት ከሆነ አንዲት እናት በቀዶ ህክምና ከተገላገለች ወዲህ በሯሷ ለመቀመጥ ይከብዳታል ምክንያቱም የ ሆድ-እቃ ጡንቻዎች በሂደቱ ስለሚደክሙ የሚል ነበር። እኔ ግን ልጄን ማየት ፈልጌያለሁ በዚያ ላይ ብቻዬን ነኝ።ስለዚህ ቀስ ብዬ ወደ ጎን ከንበል ብዬ በራሴ ለመቀመጥ ቻልኩኝ። እጄ ላይ በመርፌ የተሰካውን የ ጉሉኮስ መቆሚያ ብረት እየገፋሁ ልጄን ፍለጋ ከ ክፍሌ ወጣሁ።
የጨቅላ ህፃናት ማቆያ ክፍሉን እንዳገኘሁኝ ፤ ልጄን ለማየት በቃሁ። "አዎ ልጄ ልቅም ያልክ ፣ ምንም አይወጣልህም" አልኩኝ። የ ስድስት ወር እርጉዝ ሳለሁ ጊዜ እንደ ህልም ቢጤ ለማየት በቅቼ ነበር። ልጄ ወንድ እንደሆነ ፣ ፀጉሮቹም ለስላሳ እና ወርቃማ እንደሆኑ። አሁን ልጄን በ አይኔ ሳየሁ እንደ ህልሜ ሆኖ አገኘሁት።
ልጄን በተገላገልኩኝ ሁለተኛ ቀን ጀምሮ የ ጡቴ ወተት ይፈስልኝ ጀመር። ግን ልጄ መጥባት እንደጀመረ እጅግ የሚቃጥል ህመም ጡቴን ይሰማኝ ጀመር። ጥርሴን ነክሼ እንደምንም ልጄን ማጥባት ቀጠልኩኝ ፤ ሌላ ምርጫ የለኝምና።
አካላቴ ቀስ በ ቀስ መዳን ጀመረ ፣ አዕምሮዬ ግን አሻፈረኝ አለ።
መውለድ የህሊና ጠባሳ ጥሎብኝ አልፏል። ከዚያም በላይ በራሴ እጅግ ተበሳጭቻለሁ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ይህ ሁሉ አልበቃኝ ብሎኝ ደም ማነስ እና ድባቴም እኔው ጋር ተገኝተዋል። ባለቤቴም ደግሞ እንደ በተለመደው የማሳይ ባህል መሰረት ከወለድኩኝ በኋላ ከእኔ እርቋል። ምንም እንኳን ቢናፍቀኝም እኔ እና የአብራኩ ክፋይ ልጁን እንዴት እንኳን ትንሽ ሰዓት ሰውቶ መጠየቅ ይሳነዋል እያልኩኝ ራሴን በ ሀዘን እጠይቃለሁ።
አማቼ (የ ባለቤቴ እናት) ግን ወደ እኔ እየመጣች ትጠይቀኛለች። ማታ ማታ በተራ ልጄን ያኒክን ትይዝልኛለች ፤ ልብሱን ታጥብልኛለች። አንዳንዴም ምግብም ታበስልልኛለች። ይሄ ልማድ በማሳይ ማህበረሰብ የተለመደ ሲሆን። ወላድ አራስ ለሁለት-ሶስት ወራት ያህል ምንም ስራ እንድትሰራ አይመከርም። በምትኩም ሴት ዘመዶቿ ከጎኗ በመሆን የቤት ውስጥ ስራዎችን በመስራት ይንከባከቡአታል።\
ድሮም ቢሆን አማቼን ያያኢ የምወዳት ቢሆንም ልጄ ያኒክን ከተገላገልኩኝ ቅርበታችን በጣም ጨምሯል። እናትነት ምን ማለት እንደሆነ ፤ ምን ያህልስ ፈታኝ እንደሆነ ለማስተዋል በቅቻለሁ። ሁሉም ሴቶች በሚለግሱኝ ፍቅር እና እንክብካቤ ውስጤ መርካት ጀምሯል።
አመሰግናቸዋለሁ ብቻ ማለት ፍቅሬን ጉልበት ያሳጣዋል። ሁሌም ቢሆን ከልቤ እወዳቸዋለሁ ፣ አከብራቸዋለሁ። ምክንያቱም ደግሞ ከጎኔ ስላልተለዩ ብቻ ሳይሆን ፤ እናት ሆኜ ሳየው እናትነት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ስለተረዳሁኝም ጭምር ነው። የማሳይ እናቶች ይሄም ሳይበግራቸው እስከ አስር ልጆች አምጠው ይወልዳሉ። አማቼም ያያኢም ብትሆን ስምንት ልጆች ሲኖሯት ፤ ባለቤቴ የ በኩር ልጇ ነው።
ራሴን እና ማህበረሰቡን ላይ ባለመተማመኔ ትልቅ ስህተት እንደሰራሁ ተገልፆልኛል። ይህም በመሆኑ ቀላል የማይባል ወሊድ ላሳልፍ በቅቼያለሁ። ግን ደግሞ ነገሮች እንደዚያ ባይሆኑ ኑሮ ይሄንን ፅሁፍም ይዤላችሁ ባልቀረብኩ ነበር። ሁሉም በምክንያት ነው እንዲሉ። እጅግ ድንቅ የሆነ፣ ነፍሱ በርኅራኄ እና በፍቅር የሚያበራ ወንድ ልጅ አለኝ። ስለዚህም አመስጋኝ ነኝ። እናት በመሆኔ ሳቢያ ብዙ ነገር ለመማር በቅቼያለሁ። ሴቶች ሰውነታቸውን እንዲያምኑ ብሎም ከድራማ ሆነ ከአሰቃቂ ጠባሳ የራቀ ወሊድ እንዲገጥማቸው ማስቻል ምኞቴ ነው።
እንደ እኔ ወሊዳቸው ቀላል ያልሆነላቸውን እናቶች ከቁስላቸው እንዲያገግሙ አበክሬ እሻለሁ። ምክንያቱም ይህ ሲሆን ነው የእኔም ቁስል የሚደርቀው።
Hiwote Bekele
Wow! This is touching and so beautifully written. Thank you for sharing your story, Stephanie and Enathood for this platform!
Mohammed
This was great!