ድህረ-ወሊድ በእናትነት ጉዞ ውስጥ መነጋገር ከምፈልጋቸው አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
ምንም እንኳን እየተሻሻለ እና ሰዎች ድህረ-ወሊድን እየተገነዘቡ ቢሆንም ፣ በበቂ ሁኔታ የተነጋገርንበት እና በደንብ የተረዳንው አይመስለኝም፡፡
እውነቱን ለመናገር እኔም በደንብ የተረዳሁት አይመስለኝም። ወይም ከወሊድ በኋላ ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥያቄዎች እና ነገሮች ሁሉ መልስ አለኝ ብዬ አላስብም፡፡
ነገር ግን ውይይቱን ለመጀመር እፈልጋለሁ። ከእናንተ ሀሳብ በመስማት እና ከእርስበርስ ልምዳችን በመማማር ድህረ-ወሊድን ትንሽ ቀለል ለማድረግ እንደምንችል አስባለሁ፡፡
የራሴን ታሪኬን በመናገር ልጀምር፡፡
የመጀመሪያ ልጄን የወለድኩት በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ መሃል ላይ ነበር፡፡ ኧረ ስለአዲሱ ቫይረስ የተሻለ ባወቅንበት መሃል ላይ እንኳን አይደለም ገና በወረርሽኙ መጀመሪያ ላይ ነው ብል ይሻላል። እ.ኤ.አ. መጋቢት 2020 አጋማሽ ነበር፡፡
የምንኖርበት የቴክሳስ ግዛት ክልሉን የመዝጋት እርምጃውን ያስተላለፈው እኔ ለመውለድ ሆስፒታል ውስጥ በነበረኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በምጥ ላይ ስለነበርኩ ዜና እየተከታተልን አልነበረም፡፡ ክልሉ መዘጋቱን ማን እንደነገረን ታውቃላችሁ? ቤተሰቦች ከኢትዮጵያ ደውለው ነው የነገሩን
የእብደት ጊዜ ነበር!! የክልል መዘጋት እርምጃ ምን ማለት እንደሆነ አናውቅም። በቁም ነገር ስንወጣ ምን እንደሚጠብቀን አናውቅም ነበር !!
የወሊድ ታሪኬን በሌላ ጽሑፍ ላይ አጫውታችሁአለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በድህረ-ወሊድ ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡ ስለዚህ ልጄን ከወለድኩ በኋላ እና ከሆስፒታል ከወጣን በኋላ ስለ ወረርሽኙ እና የክልል የመዘጋት እርምጃ ምን ማለት እንደሆነ መማር ጀመርን፡፡
ግራ አጋቢ ነበር (ቢያንስ ለእኔ) እና በጣም ብዙ እርግጠኛ ያለመሆን እና አለመረጋጋት ነበር፡፡ ቀናት እያለፈ ሲሄድ ፍርሃቱ እና ውጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ፡፡ ጓደኞች ወደ ቤታችን መምጣታቸውን አቆሙ፡፡ ቤተሰቦቻችን እኛን ሊጎበኙን የነበረው የጉዞ ዕቅድ ሁሉ ተሰረዘ፡፡ ወደ ገበያ መውጣት አስፈሪ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ይመስገን የምንፈልገውን ሁሉ ቤት ድረስ እንዲመጣልን ማድረግ የምትችልበት ሀገር ውስጥ በመኖራችን፡፡ እንደ እኔ በተመሳሳይ ጊዜ ለወለዱ ሴቶች እና በወረርሽኙ ምክንያት በተከሰቱት መዘዞች ሁሉ ለተጎዱ ልቤ በጣም ያዝናል፡፡
ቤተሰቦቻችንን እና ጓደኞቻችንን ለማነጋገር የቀረን የስልክ ጥሪ ብቻ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂን ያመሰገንበት አንዱ ጊዜ ይሄ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፣ ትናንሽ ነገሮችን ማድነቅ እና አመስጋኝ መሆንን ተማርን። ወረርሽኙ አስተማሪም ነበር፡፡
ልጅ መውለድ ፣ ሰውን ወደ ህይወታችን ፣ ወደ ቤታችን ፣ ወደ ዕለታዊ ተግባራችን ማምጣት በጣም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ እራሱን የቻለ ሂደት ነው፡፡ በበረከት እና በደስታ የተሞላ ነው። ነገርግን ቀላል አልነበረም። ብዙ ስራ አለው እና ብዙ ማስተካከያዎችን ይጠይቃል።
“ልጅን ለማሳደግ አንድ መንደር ያስፈልጋል” ይባላል፡፡ በዚያ ጊዜ ለእኛ እንኳን አንድ መንደር የቅርብ ቤተሰብ እና ጓደኛ እንኳን አልነበረም፡፡
ደግሞም “ቀናቶች ረጅም ናቸው፣ ዓመታት ግን አጭር ናቸው” ይባላል፡፡ በጣም እውነት ነው!! በድካም ፣ በህመም ፣ ወይም በማልቀስ ያሳለፍኩአቸው ብዙ ረጅም ቀናቶች ቢኖሩም አመቱ እንዴት እንደበረረ ግን አልታወቀኝም፡፡
አሁን የልጃችንን የመጀመሪያ ልደት አክብረን ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖናል። እናም እኔ እና ባለቤቴ ወላጆች ከሆንን በአንድ ዓመት እና በጥቂት ወሮች ውስጥ ብዙ ተምረናል አድገናል፡፡
እንዲሁም የወረርሽኙ ጊዜ ነገሮችን ከተለየ እይታ ማየት የተማርንበት ነበር፡፡ የተከሰተው ወረርሽኝ ለእኛ ቤተሰብ ዕድሎችን ሰጥቶናል። ባለቤቴ ከቤት መሥራት በመጀመሩ ልጃችንን ጎን ለጎን አንድ ላይ ለማሳደግ እድል አግኝተናል፡፡ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው!! እናም ሁልጊዜ ተመስገን እንላለን፡፡
ማማ ለድህረ-ወሊድ እንዴት እንደምትዘጋጂ ፣ ምን መጠበቅ እንዳለብሽ ፣ ለእኔ ምን እንደረዳኝ እና አንዳንድ ኃይል ሰጪ አበረታች ሀሳቦችን በዚህ ፅሁፍ ይዤ መጥቻለሁ፡፡
ድህረ-ወሊድ ምንድነው? ምን ይመስላል? እና ምን መጠበቅ አለብሽ?
ድህረ-ወሊድ በአጭሩ ከወሊድ በኋላ ያለው ጊዜ ማለት ነው፡፡ ልጅ መውለድ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ፣ ከወሊድ በኋላ ያለው ጊዜ ለእናት ማገገም ወሳኝ እንደሆነ ያውቃል፡፡
በጥንታዊ ባህሎች ወስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በድህረ-ወሊድ ወቅት እናቶችን የመንከባከብ ባህል አለ፡፡ በአብዛኞቹ እነዚህ ሀገሮች ውስጥ እናት ቢያንስ ለ40 ቀናት ትታረሳለች ፣ ታርፋለች፡፡ ቤተሰቦች ፣ ዘመዶች እና ጓደኞች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ይሰራሉ ፣ አዲሱን ሕፃን በመያዝ ይረዳሉ ፣ ለወለደችው እናት ገንቢ ምግቦችን ያዘጋጃሉ፡፡
አብዛኞቻችን በምዕራባውያን አገሮች የምንኖር እንደዚህ ዓይነት ቅንጦት አናገኝም፡፡ ይህ በድህረ-ወሊድ ጊዜ ከሚያጋጥሙን ሌሎች ችግሮች ላይ ተጨማሪ ይሆናል፡፡
ድህረ-ወሊድ በመሠረቱ ከወሊድ በኋላ ማገገም ነው፡፡ ነገር ግን ከወሊድ በኋላ ሊከሰቱ ከሚችሉ ከአንዳንድ የጤና ችግሮች ጋር ሊመጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ድብርትን ጨምሮ ስሜታዊ እና ሆርሞናዊ ለውጦችን ሊያካትት ይችላል፡፡ ከዚህ በታች ሁሉንም አንድ በአንድ እንመልከት።
ሎቺያ (Lochia)
ሎቺያ ከተወሊድ በኃላ ልጁን በማህጸን ወስጥ አቅፎ የያዘው የማህፀን ግርግዳ ህዋሳት መፍረስ እና የማህፀን ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለሰ በሚያደርገው መሰብሰብ ምክንያት የሚከሰት የደም መፍሰስ እና ተያያዥ ፈሳሽ ነው፡፡ ይሄ ከወር አበባ ጊዜ የተለየ ነው ፣ በምጥም ሆነ በቀዶ ጥገና ቢወለድ ሎቺያ ይኖራል ፡፡
- የደም መፍሰስ መጀመሪያ ላይ ከባድ ሊሆን ይችላል እና ከጊዜ በኋላ እየቀነሰ ይሄዳል
- የደም መፍሰሱ እሰከ 6 ሳምንታት ሊቆይ ይችላል
- በሎቺያ ውስጥ የረጋ የተቋጠረ ደም ማየት ይኖራል፡፡ አነስተኛ እና ተደጋጋሚ እስካልሆነ ድረስ ችግር የለውም።
- የብልት ፈሳሽ ቀለም ቀስ በቀስ ከቀይ ወደ ቡናማ ከዛም ወደ ነጭ ይለወጣል።
ድንገተኛ ከባድ የደም መፍሰስ ካለሽ ወይም አንድ ወይም ከአንድ በላይ የንፅህና መጠበቂያ ጨርቅ በአንድ ሰዓት ውስጥ ከረጠበ ፣ ከቴኒስ ኳስ የሚበልጡ የረጋ የተቋጠረ ደም ካየሽ እና ከባድ የሆድ ህመም ወይም ቁርጠት ካለሽ የጤና እርዳታ ማግኘት አለብሽ፡፡
ከወሊድ በኋላ ህመም
ማህፀን ወደ ቅድመ-እርግዝና መጠን ይመለሳል። ስለሆነም የምጥ አይነት ስሜት ሊሰማሽ ይችላል። ይሄም ከወሊድ በኋላ ህመም ማለት ነው፡፡
ህመሙ ከምጥ ቀለል ያለ ነው። ጡት በምታጠቢበት ጊዜ ትንሽ ጠንከር ብሎ ሊሰማሽ ይችላል። ምክንያቱም ጡት በማጥባት ጊዜ ከሚለቀቁት ሆርሞኖች ጋር ስለሚገናኝ ነው፡፡
ማህፀንሽ በ6 ሳምንታት ውስጥ ወደ ቅድመ-እርግዝና መጠን ይመለሳል፡፡ የሕመሙ ጥንካሬ ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ከወሊድ በኋላ ህመምን ቀለል ለማድረግ እነዚህን አድርጊ ፡ -
- የምጥ ጊዜ የትንፋሽ ቴክኒኮችን መጠቀም
- ጡት ከማጥባትሽ በፊት ሽንት መሽናት እና ፊኛን ባዶ ማድረግ
- በሆድዎ ላይ የሚሞቅ ነገር መያዝ
- የህመም ማስታገሻ መድሃኒት መውሰድ (ለጡት ማጥባት ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አረጋግጪ)
የሆድ ድርቀት እና ኪንታሮት
የሆድ ድርቀት መኖር የተለመደ ነው፡፡ የሆድ ድርቀት ኪንታሮት ሊያስከትል ወይም ሊያባብሰው ይችላል፡፡ ሆድ ማለስለሻ መድሀኒት መጠቀም ወይም አመጋገብን መቀየር ይረዳል፡፡
ኪንታሮት የተለመደ በእርግዝና ጊዜ እና ከወሊድ በኋላ ሊከሰት የሚችል ፊንጢጣ ውስጥ የሚያድጉ ጅማቶች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጨ ተልባ ተዘጋጅቶ በእርግዝና የመጨረሻ ወራቶች እና ከወሊድ በኋላ ለእናቶች እንዲጠጡ የሚደረግበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የሆድ ድርቀት እና ኪንታሮትን ለመከላከል ወይም ለማስታገስ ይረዳሉ፡-
- ብዙ ውሃ መጠጣት
- ብዙ ገለባ ያላቸው (fiber) ምግቦችን እንደ፡- አትክልቶች ፣ ፍራፍሬዎች ፣ ያልተፈተጉ እህሎች (whole grain) መመገብ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የተልባ ወይም የቺያ ዘሮችን (chia seeds) ምግብሽ ውስጥ ማካተት ትችያለሽ፡፡
- የመፀዳዳት ፍላጎት ሲመጣ አለማቆየት፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ይዞ መቆየት የሆድ ድርቀት የመከሰት እድልን ከፍ ያደርጋል፡፡
የቁስል መመርቀዝ /ኢንፌክሽን (infections)
ከወሊድ በኋላ የኢንፌክሽን የመፍጠር ከፍተኛ እድል አለ፡፡ የብልት አካባቢን ፣ ከወሊድ በኋላ ስፌት (stitches) ካለ ወይም በቀዶ ጥገና ከወለድሽ የተሰፋውን ቁስል መከታተልና መንከባከብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ኢንፌክሽኖችን ለማስወገድ ይህንን አድርጊ ፡-
- ዶክተር ያዘዘውን መድሃኒት በትክክል መውሰድ
- በሲትዝ / ኤፕሰም (sitz/epsom) ጨው ገንዳ መዘፍዘፍ ወይም በሰሐን ላይ ሲትዝ / ኤፕሰም ጨውና ሞቅ ያለ ውሃ ላይ አድርጎ መቀመጥ
- ከመፀዳዳት በኋላ ከፊት ወደኋላ መጥረግ። እንዲሁም ከሽንት በኋላ የብልት አካባቢን ለማፅዳት ሞቅ ያለ ውሃ መጠቀም፡፡ ይህ ስፌቶች (stitches) ካለ በተለይ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
- ታምፖኖችን ወይም የወር አበባ ኩባያዎችን (tampon or menstrual cups) አለመጠቀም፡፡ ከጥጥ / ከጨርቅ የተሰራ የንፅህና መጠበቂያ ብቻ መጠቀም፡፡
- የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመቀጠል ቢያንስ ለ6 ሳምንታት መጠበቅ፡፡ የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመቀጠል በፊት ሐኪምን ማማከር እና ምርመራ ማድረግ ይመከራል፡፡
የኢንፌክሽን ምልክቶች
- ሎቺያ ከመጥፎ ሽታ ጋር ማየት
- የ 100.4 ℉ (38 ℃) ወይም ከዚያ በላይ የሰውነት የሙቀት መጠን
- በስፌት (stitches) ዙሪያ ካለው አካባቢ ፍሳሽ መጨመር (ስፌት ላላቸው እናቶች)
- በቀዶ ጥገናው ጠርዝ ዙሪያ የደም መፍሰስ ፣ ፈሳሽ ፣ ማበጥ ፣ መከፈት (በቀዶ ጥገና ለወለዱ እናቶች)
ከወሊድ በኋላ ፕሪኤክላምሲያ (Postpartum Preeclampsia)
ከወለዱ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 48-72 ሰዓታት ውስጥ ሊከሰት የሚችል ያልተለመደ ሁኔታ ነው፡፡ በጣም አልፎ አልፎ ፕሪኤክላምሲያ ከወሊድ በኋላ እስከ 4-6 ሳምንታት ድረስ ሊከሰትም ይችላል፡፡
የድህረ ወሊድ ፕሪኤክላምሲያ ምልክት
- ድንገተኛ የፊት ወይም የአካል ክፍሎች እብጠት
- ከፍተኛ የደም ግፊት
- ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ
- ከባድ ራስ ምታት
- በጣም ትንሽ ሽንት
- ድንገተኛ የትንፋሽ ማጠር
ማንኛውም አይነት የኢንፌክሽን ወይም ፕሪኤክላምሲያ ምልክት ካለሽ የጤና ባለሙያ ማግኘት እና መታከም አለብሽ።
ከወሊድ በኋላ የአካል ለውጥ
ማማ ፣ ከወሊድ በኋላ ስለራስሽ በአእምሮሽ ውስጥ ያለው የሰውነት ምስል እንደበፊቱ ላይሆን ይችላል። ሆኖም ሰውነትሽ እንዳለው ውብ መሆኑን እወቂ፡፡ ውድ ልጅሽን ለማሳደግ ሰውነትሽ ከዘጠኝ ወራት በላይ በጣም ጠንክሮ እየሰራ ነበር፡፡ ይህ አካል ልጅሽን የጠበቀና የተንከባከበ አካል ነው፡፡
ሰውነትሽ ሕይወትን ሰጥቶአል!!
ስለ ሰውነትሽ አመስጋኝ መሆን እና ሙለ በሙሉ መቀበል አለብሽ፡፡
የክብደት መጨመር ፣ ወይም የሸንተረር ምልክት ፣ ወይም የፀጉር መርገፍ እና በሰውነትሽ ላይ ያሉ ማናቸውም ሌሎች ለውጦች ከልጅሽ ፍቅር በጭራሽ አይበልጡም፡፡
ከወሊድ በኋላ ያለሽበትን የሰውነት ክብደት ወይም ቅርፅ ካልወደድሽው በመጀመሪያ ታርሰሽ ጨርሺ ፣ ከዚያ በኋላ ክብደትሽ ላይ ለመስራት ጊዜ ታገኛለች፡፡ ካስፈለገሽ ደግሞ ከረጅም የጡት ማጥባት ጥቅሞች መካከል አንዱ የእርግዝና ክብደትን ለመቀነስ መርዳቱ ነው፡፡ ስለዚህ በማጥባት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ትችያለሽ።
የድህረ ወሊድ ስሜቶች እና ሆርሞኖች
ከወሊድ በኋላ መከፋት (postpartum/baby blues)
ከወሊድ በኋላ መከፋት ህፃኑ ከተወለደ በኋላ የጭንቀት ፣ የሀዘን ፣ የብቸኝነት ፣ የድካም ወይም የማልቀስ ስሜት ያጠቃልላል፡፡
ማማ ስሜታዊ መሆን ሊኖር ይችላል፡፡ የሆርሞኖች መለዋወጥ ፣ የእንቅልፍ መዛባት ፣ እና ከወለድ በኋላ ህመም ፣ በተጨማሪ ለልጅሽ ፍላጎቶች ሁሉ ምላሽ መስጠት አለ፡፡ ጊዜ ሰጭው፡፡ እነዚህ ስሜቶች ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በራሳቸው ያልፋሉ፡፡
ከወሊድ በኋላ የመከፋት ስሜት አጋጥሞኛል፡፡ ለሦስት ቀናት ረዥም የወሊድ ምጥ ስለነበረኝ በጣም ደክሞኝ ነበር፡፡ እና ደግሞ ከስፌቶቼ የተወሰነ ህመም ነበረኝ፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት ስለ ኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ስለ አጠቃላይ ጊዜው አዝኜ እና ግራ ተጋባቼ ነበር፡፡ እናም በመጀመሪያዎቹ ሳምንቶች የልጄን ፍላጎቶች ሁሉ ማሟላት ቀላል አልነበረም፡፡
እኔ ፣ ባለቤቴ ፣ እና ልጃችን ቀስ በቀስ ተረዳድተን ለጉዳዮቹ አንድ በአንድ መፍትሄዎችን አገኘን፡፡ ማንበብሽን ቀጥይ፣ ምን እንደረዳኝ እና ከልምዶቼ ያገኘኋቸውን ትምህርቶች እገልፃለሁ፡፡
ከወሊድ በኋላ ድብርት (Postpartum Depression)
ከላይ እንደተጠቀሰው አንዲት እናት ከወሊድ በኋላ የመከፋት ስሜትን ማየቷ የተለመደ ነው፡፡ ከወሊድ በኋላ የመከፋት ምልክቶች በተቃራኒ እንደ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ድብርት በራሱ አይሄድም፡፡ ልጅ ከወለዱ በኋላ ለቀናት ወይም ለወራት ሊታይ ይችላል። ሕክምና ካልተደረገለት ለብዙ ሳምንታት ወይም ወራት ይቆያል፡፡ ከወሊድ በኋላ ድብርት ቀኑን በሰላም ማሳለፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም ልጅሽን እና ራስሽን የመንከባከብ ችሎታሽ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
በአሜሪካ የሥነ-ልቦና ማህበር (APA) መሠረት ከ 7 ሴት 1 በጣም ከባድ የስሜት መቃወስ ያጋጥማቸዋል ወይም ከወሊድ በኋላ ድብርት ይገጥማቸዋል።
ከ 7 ሴት 1 !! ይህ ማለት አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ በብዙዎቻችን ላይ ሊሆን ይችላል ወይም ቀድሞውኑም ተከስቷል ማለት ነው፡፡
ከወሊድ በኋላ ድብርት ከወሊድ በኋላ የሚመጣ የስነልቦና በሽታ ነው ፣ እንደ ሕልሞች ወይም የሌሉ ነገሮችን ማየት ያሉ የስነልቦና ምልክቶችን ሊያካትት የሚችል ሁኔታ ነው።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ድብርት በማንኛዋም እናት ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ ቀላል እርግዝና ወይም ከባድ እርግዝና ያላቸው ሴቶች ፣ የመጀመሪያ ጊዜ እናቶች እና እናቶች አንድ ወይም ከዚያ በላይ ልጆች ያሏቸው ፣ ያገቡ ሴቶች እና ያላገቡ ሴቶች ፣ እና ገቢ ፣ ዕድሜ ፣ ዘር ወይም ጎሳ ፣ ባህል ወይም ትምህርት አይለይም፡፡
የወሊድ በኋላ ድብርት ምልክቶች
- ከመጠን በላይ ጭንቀቶች እና ፍርሀት
- ቀድሞ በሚዝናኑባቸው ነገሮች ደስታ አለማግኘት
- ከመጠን በላይ ማልቀስ እና ሀዘን
- ቢደክምሽም እንኳ መተኛት አለመቻል
- የምግብ ፍላጎት መቀየር
- ልጅሽን ወይም ራስሽን ለመጉዳት ማሰብ
- የሌሉ ነገሮችን ማየት መጀመር
እኔ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከወሊድ በኋላ መከፋቴ እየደበዘዘ ስለሄደ ከወሊድ በኋላ ድብርት የነበረኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ ከወሊድ በኋላ በድብርት የሚሰቃዩ እናቶችን ሁኔታ እረዳለሁ። ምንም እንኳን ከባድ የወሊድ በኋላ ድብርት ምልክቶች ባይኖርብኝም ፣ ወይም ያጋጠመኝ ነገር ለረጅም ጊዜ ያልዘለቀ ቢሆንም ሁላችንም እናቶች በተወሰነ ደረጃ ከወሊድ በኋላ ድብርት እንደሚኖረን አምናለሁ፡፡
በብዙ ባህሎች ውስጥ ዝቅተኛ ግንዛቤ እና የአእምሮ ህመም ላይ ማግለል በመኖሩ ምክንያት ፣ አብዛኛዎቹ የወሊድ በኋላ ድብርት ጉዳዮች በጭራሽ ሪፖርት ሳይደረጉ ይቀራሉ፡፡ ወይም እንደ ችግር እንኳን ለይተን ሳናውቀው እና እርዳታ ሳናገኝ እንቀራለን፡፡
ከወሊድ በኋላ ድብርት አለኝ ብለሽ ካሰብሽ ወይም አንዳንድ ምልክቶችን ካስተዋልሽ የጤና ባለሙያ እንድታነጋግሪ አሳስባለሁ፡፡ ወይም ስለ ስሜቶችሽ ለቤተሰብ እና ለጓደኞች መናገር። እርዳታ ለማግኘት የሚያስፈልግሽን ማንኛውም ነገር ሁሉ አድርጊ። ከአለፈ በኋላ በችግር ከማዘን ይልቅ ደህንነትን ማስቀደም የተሻለ ነው!!
የእኔ ሀሳቦች እና በድህረ-ወሊድ ወቅት ጊዜ የረዱኝ ነገሮች
- አስፈላጊ ከወሊድ በኋላ መልሶ ማገገሚያ ኪት
ራስሽን በአግባቡ ለመንከባከብ ፣ ኢንፌክሽኖችን ለማስወገድ እና ከወሊድ በኋላ ህመምን ለመቀነስ ከወሊድ በኋላ የማገገሚያ አስፈላጊ ነገሮችን በቅድሚያ አዘጋጅተሽ አስቀምጭ፡፡ እኔ የፍሪዳ (Frida’s) የድህረ-ወሊድ ኪት ተመችቶኝ ነበር፡፡ የዚህ ኩባንያ ስብስብ በአንድ ጥቅል ውስጥ የሚያስፈልግሽን ሁሉ ያካትታል፡፡
- የምግብ ቅድመ ዝግጅት ወይም በብዛት ምግብ ማብሰል
ከተቻለ በእርግዝናሽ የመጨረሻ ቀናት ምግብ ቀድመሽ ማዘጋጀት ፣ ማብሰል ፣ እና ማስቀመጥ፡፡ ካልሆነ ጊዜ ባገኘሽ ቁጥር በዛ አድርጎ ምግብ ማብሰል፡፡ እያንዳንዱን ቀን ከማብሰል ይልቅ ለጥቂት ተጨማሪ ቀናት እንድትጠቀሚበት ይረዳሻል፡፡
- ሁሉን ነገር ማድረግ እንደማትችይ እወቂ
ይሄን ምነው አንድ ሰው ቀደም ብሎ በነግረኝ፡፡
እንደ ሴት ሁሉንም ነገር እናደርጋለን፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ፣ ልጃችንን መንከባከብ ፣ ባለቤታችን መንከባከብ ፣ የስልክ ጥሪዎችን መመለስ ፣ ወዘተ እና ሁሉም ነገር ላይ እንከን የሌለው ለመሆን እንፈልጋለን፡፡
ማማ እስቲ ልንገርሽ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ማድረግ አትችይም። ማድረግም ግዴታ አያስፈልግሽም!! እና ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ መስጠት ጥሩ ነው፡፡ አንቺም ሰው ነሽ። እንደማንኛውም ሰው ይደክምሻል። እና ደግሞ ገና ልጅ መውለድሽ ነው፡፡ ከምንም በላይ ማረፍ ያስፈልግሻል!!
ከእናትነት ጋር ለመላመድ ጊዜ ያስፈልግሻል፡፡ ከአዲስ ልጅሽ ጋር ለመግባባት ጊዜ ያስፈልግሻል፡፡ ከወላጅነት ጋር ለመላመድ እንኳን ከባለቤትሽ ጋር ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ እሱም እራሱ ገና አባት መሆኑ ነው፡፡ ሁለታችሁም ማን ምን እንደሚሰራ ለማወቅ እና ሀላፊነቶችን ለመከፋፈል ጊዜ ያስፈልጋችኋል፡፡
ምንም እንኳን የመጀመሪያ ጊዜሽ ባይሆምን 2ተኛ ወይም 3ተኛ ወይም ሌላ ማንኛውም ቁጥር ልጅ ብትወልጂም አንድ አዲስ ሰው በቤተሰብ ውስጥ እየተጨመረ ስለሆነ ነገሮች ለማስኬድ እና ለማስተካከል ጊዜ ያስፈልጋል፡፡
- እርዳታ መጠየቅ ጥሩ ነው
ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች እርዳታ ለመጠየቅ ወይም ሌሎች እርዳታ ሲያደርጉ ለመቀበል ይቸገራሉ፡
እውቱን ልናገር እኔም በዚህ እቸገራለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም እርዳታ መጠየቅ ያስቸግራል። ነገር ግን የተማርኩት ነገር እርዳታ መጠየቅ ወይም መቀበል ጥሩ ነው፡፡
ማማ ልንገርሽ አንድ የሚያስፈልገሽ ቀን ይኖራል፡፡ አስታውሺ እርዳታ መጠየቅ ወይም መቀበል ችግር የለውም!! ስለዚህ ለጓደኛሽ ወይም ለቤተሰብሽ አባላት ደውይ እና የምትፈልጊውን ጠይቂ፡፡
ምን እንደሆነ ታውቅያለሽ? ብዙ ጊዜ የምትፈልጊውን ታገኛለሽ፡፡ ብዙ ሰዎች አዲስ እናትን ለመርዳት ደስተኞች ናቸው፡፡
አንድ ቀን አስታውሳለሁ ሀገር ቤት ኢትዮጵያ እንደምናደርገው በሣህን የታሰረ የድግስ የተፈተፈተ እንጀራ አማረኝ። ለድግስ ከተዘጋጀ ሁሉም ዓይነት ምግብ በምሳ ዕቃ ውስጥ ተደርጎ ለትላልቅ ሰዎች ወይም ድግሱ ላይ ላልተገኙ ሰዎች ታስሮ የሚላከው ትዝ ይላችሁአል?
ብዙ ጊዜ ከአያቴ ጋር አብረን ስንበላ ትዝታዎች አሉኝ፡፡ እናም አንድ ቀን ለምን እንዳስታወስኩ አላውቅም አማረኝ፡፡ ከዛ በጥሩ ሁኔታ ያማረኝን እንደምታዘጋጅል የማውቃት ሰው ጋር ደወልኩ፡፡ እርሷም በመደወሌ በጣም ደስተኛ ነበረች ምክንያቱም ሁልጊዜም ለመርዳት ትጠይቅኝ ነበር፡፡ ባለቤቴ ወደ ቤቷ ሄዶ አመጣልኝ፡፡ እንዴት ደስ ብሎኝ እንደበላሁ አልረሳውም።
- እራስሽን ተንከባከቢ
ማማ ልጅሽን እንደምትንከባከቢው ሁሉ እራስሽንም መንከባከብ ያስፈልግልሻል፡፡ ጥሩ እናት መሆንና ለልጅሽ መልካሙን ሁሉ ማድረግ የምትችይው ደህና ስትሆኚ ብቻ ነው፡፡
በእርግዝና ወቅት እንደምትመገቢው ሁሉ ጤናማ አልሚ ምግቦችን መመገብ አለብሽ፡፡ ሰውነትሽ አሁንም በጡት ወተትሽ በኩል ህፃን እያሳደገ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጡት ባታጠቢም ከወሊድ በደንብ ለማገገም ለሰውነትሽ ምግብ ያስፈልግሻል፡፡ በአልጋሽ አጠገብ ቀለል ያሉ ምግቦችን አስቀምጪ፡፡ ገንቢ ምግብ ተመገቢ፡፡ ብዙ ፈሳሽ ጠጪ፡፡
በቂ እንቅልፍ መተኛት ያስፈልግሻል። ይሄ በጣም ትኩረት እንዲሰጠው እፈልጋለሁ፡፡ አስቸጋሪ እንደሆነ አውቃለሁ እና ከህፃኑ ጋር አዳዲስ ነገር ይኖራል። ነገር ግን ለእንቅልፍ ጊዜ መፈለግ አለብሽ፡፡ እንዲሁም ህፃኑ ሲተኛ አብረሽ መተኛት ትችያለሽ፡፡ ያልታጠበ የእቃ ክምር ወይም የቆሸሸ ልብስ ብዛት እንዳለ መቆየት ይችላል!! አሁን እራስሽን አሳርፊው እና በኋላ ላይ ለሁሉም ትደርሻለሽ፡፡
ከልጅሽ ጋር አብረሽ ገላሽን መታጠብ፡፡ ከአራስ ልጅ ጋር መታጠብ አስፈሪ ሊመስል ይችላል ግን እመኚኝ እና ሞክሪው። ማድረግ ትችያለሽ። በጣም ደስ ይላል !!
እኔም ለመሞከርም ፈርቼ ነበር። ነገር ግን አንዴ ከሞከርኩ በኋላ ልጄን ብቻውን አጥቤው አላውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንኳን ከአባቱ ጋር አብረን ሶስት ሆን እንታጠባለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ህፃኑን ለአባቱ አስይዘሽ ፣ ወይም ህፃኑ ሲተኛ ፣ ወይም የሆነ ሰው ልጅሽን ለተወሰነ ጊዜ ሲይዝልሽ ፣ ለብቻሽ ሞቅ ባለ ውሃ ገላሽን ለብቻሽ መታጠብ ፣ ከተቻለ በገንዳ ውስጥ መዘፍዘፍ እና እራስሽን ዘና ማድረግ፡፡ (የዕፅዋት መታጠቢያ ፣ ኤፕሰም ጨው ቁስልሽን ለማዳን ይረዳል)
- አሉታዊነትን ሀሳቦችን ማስወገድ
ከላይ እንደጠቀስኩት ከወሊድ በኋላ ስሜታዊ መሆን ሊኖር ይችላል። መውለድ በህይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ነው። ጉልበትሽን የሚያባክን አሉታዊ ወሬ ፣ ዜና ፣ ድራማ ፣ ወዘተ አያስፈልጉሽም። ከአዲሱ ልጅሽ ጋር ውድ ጊዜሽን በደስታ እና ከልጅሽ ጋር እቅፍቅፍ ብለሽ በፍቅር አሳልፊ !!
ከላይ እንደገለጽኩት በኮረና ወረርሽኝ መጀመሪያ ላይ ስለወለድኩ በጊዜው ከዜና መራቅ ከባድ ነበር፡፡ ከመጠን በላይ እንድጨነቅ ያደርገኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
አንድ ምሽት መጥፎ ቅዠት አይቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ወዲያው በየቀኑ ዜናዎችን መከታተል እና እኔ ልቆጣጠረው ስለማልችለው ነገር መጨነቅ እንደማያስፈልገኝ በፍጥነት ተገነዘብኩ፡፡
ስለዚህ ከዛ ቀን በኋላ ዜናውን ማየቴን አቆምኩ ፣ ከፍርሀት ይልቅ እውነታዊ መረጃ ላይ አተኮርኩ ፣ እና በእኔ ቁጥጥር ውስጥ ማድረግ የምችላቸውን ነገሮች አደረግሁ ፡፡
እንዲሁም አዝናኝ ነገሮችን ማየት ፣ አነሳሽ እና አነቃቂ ኦዲዮዎችን ማዳመጥ ፣ እና አጭር የእግር ጉዞ ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ይሄም ትኩረቴን ለመለወጥ እና ጉልበቴን ለመሰብሰብ በጣም ረድቶኛል፡፡
- ከህይወት አጋርሽ ጋር መነጋገር ወይም እናቶች ቡድን ወስጥ መግባት
ማማ ደጋግሜ እንዳልኩት ስሜታዊ መሆን የተለመደ ነው፡፡ ሰውነትሽ በብዙ ለውጥ ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ ከህይወት አጋርሽ ጋር ስለ ስሜቶችሽ ማውራት ሊረዳ ይችላል፡፡ ባለቤቴ ለእኔ እንደ ቴራፒስትዬ ነው፡፡ ሁልጊዜ አነጋግረዋለሁ፡፡ ማውራታችንም እርስ በእርሳችን በተሻለ እንድንግባባና በግንኙነታችን ውስጥ እንድናድግም ረድቶናል፡፡
እኔ ደግሞ በመስመር ላይ (online) የእናቶች ቡድን አለኝ፡፡ በኢንስታግራም ላይ የምከታተላቸው እናቶች እና ሁለት የፌስቡክ ቡድኖች አሉኝ። ይህም ከእናቶች እንድገናኝ እና መረጃ እንዳገኝ ረድቶኛል፡፡ እናትHood እንዲሁ በዚያ መንገድ እንደሚያገለግል ተስፋ አደርጋለሁ።
በመጨረሻም ማማ በድህረ-ወሊድ ወቅት የምታሳልፊው አስቸጋሪ ሁሉ ነገር ለዘላለም አይቆይም፡፡ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ አተኩሪ እና እራስሽን ተንከባከቢ፡፡ ከላይ ያሉት ሁሉም መረጃዎች እንደሚረዱሽ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከልጅሽ ጋር አስደሳች ጊዜ እና በፍጥነት እንድትበረቺ መልካም ምኞቴ ነው፡፡
ከወሊድ በኋላ ስላጋጠሙሽ ልምዶች እና ምን እንደረዳሽ ከዚህ በታች ባለው አስተያየት ሳጥን ውስጥ አሳውቁኝ፡፡
ምንጭ:-
- INJOY የጤና ትምህርት
- የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማህበር
Hellina Woldu
I’m not a mother yet but reading your blogs will surely come in handy sometime in the future. I found this to be really educational please keep up the good job 🙌🏿👏🏾
ሐና ኃይሌ
Thank you!! for your comment.
Stay tuned, will have more useful contents.
Rekik
This made me look back to my postpurtum days. It sure is the most exciting yet, tiresome and overwhelming moment of my life. The good thing is, as you said, it won’t last forever. On top of that, the reward is a million fold worth it. Thank you for sharing this dear, it’s a topic moms need to discuss about.
ሐና ኃይሌ
Thank you!! for the feedback.
As you said we have to talk about postpartum often. I will have more contents about postpartum in the future.