ምንም እንኳን ሰዎች የጡት ማጥባት ጥቅሞችን ሙሉ በሙሉ ባይክዱም ፤ ጡት ማጥባት ለህፃኑ እድገት አይበቃም ብለው ስለሚያስቡ ልጄን የዱቄት ወተት (ፎርሙላ) በተጨማሪ እንድሰጠው በብዙ አጋጣሚዎች አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡
ስለ የእናት ጡት ወተት አስደናቂ ጥቅሞች ሳይንስ ምን እንደሚል በታትን እንመልከት፡፡ እኔም እስካሁን ድረስ በልጄ ላይ ያየሁትን ጥቅሞች እነግራችሁአለሁ፡፡
ሁሉም ሰው ጥሩ ምግብ እንደሚያስፈልገው የታወቀ ነው፡፡ በተለይ ለህፃናት እና ለልጆች የበለጠ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በትክክል ለማደግ ጥሩ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የጡት ወተት ከምግብ በላይ ነው፡፡
የጡት ወተት በአስፈላጊ የምግብ እና ባዮአክቲቭ (bio-active factor) ንጥረ ነገሮች የበለፀገ ነው። ይህም በሕይወት ለመኖር እና ለጤናማ እድገት ጠቃሚ ያደርገዋል። (ምንጭ)
በተጨማሪም ህፃናትን ከህመም ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ እንዲሁም ምቾት ይሰጣል። በእናት እና በልጅ መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል፡፡
ጡት ማጥባት የሚያስገኘው ጥቅም በአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ (AAP) እና በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በሚገባ የተመሰከረለት ነው፡፡
ሁለቱም AAP እና WHO ህፃኑ ከተወለደ በኋላ በ1 ሰዓት ውስጥ ጡት መጥባት እንዲጀምር ፣ ለ6 ወራት ጡት ብቻ እንዲጠባ ፣ እና ቢያንስ ለ1 ዓመት ያህል ወይም እስከተቻለው ድረስ ጡት መጥባቱን እንዲቀጥሉ ይመክራሉ፡፡ እንዲሁም ብዙ ጥናቶች እየወጡ የጡት ማጥባትን ጥቅሞች እያረጋገጡ ናቸው፡፡
እንዲሁም ብዙ ጥናቶች እየወጡ የጡት ማጥባትን ጥቅሞች እያረጋገጡ ናቸው፡፡ እስኪ ከዚህ በታች አንድ በአንድ እንመልከት።
ጡት ማጥባት ለህፃናት ያለው ጥቅም
እንገር የህፃናትን የበሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ያደርጋል፡፡
እንገር ለልጅሽ የመጀመሪያ ምግብ ነው፡፡ ከተወለድሽ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ቀናት (ከ2-5 ቀናት) ጡትሽ የሚኖረው እንገር ብቻ ሲሆን ይህም ለልጅሽ የሰውነትን በሽታ የመከላከል ስርዓት ለመገንባት የሚረዱ ብዙ በሽታ ተከላካይ (antibodies) ንጥረ ነገሮችን ይይዛል፡፡(ምንጭ)
ለልጅሽ ተፈጥሯዊ ክትባት እንደመስጠት ነው፡፡
በተጨማሪም እንገር ሆድን የማለስለስ ችሎታ ስላለው ህፃኑ እንዲፀዳዳ ይረዳዋል፡፡ በተለይም የመጀመሪያው እንደ ሬንጅ የመሰለ ጥቁር ቆሻሻ (meconium) ለማስወፈድ ይረዳል። ይህ ቆሻሻ ህፃኑ ከመወለዱ በፊት በሆዱ ውስጥ የሚከማች ነው፡፡
ሌላው እንገር በወፍ በሽታ (jaundice) የመያዝ እድሉን ዝቅ ያደርገዋል። የወፍ በሽታ የህፃናትን ቆዳ እና አይኖች ቢጫ የሚያደርግ ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት ፍጹም ጥሩ ሆኖ የተዘጋጀ ፣ የተሟላ ምግብ ፣ እና የህፃኑን የአመጋገብ ፍላጎቶች ለማርካት በመደበኛነት የሚለዋወጥ ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት ህፃኑ ለማደግ የሚያስፈልገውን ከፕሮቲን ስብ ፣ ካርቦሃይድሬት ፣ ውሃ ፣ እስከ ሆርሞኖች ፕሪባዬቲክስ (prebiotics) ፣ እና በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን አቀናብሮ ይይዛል፡፡
አስገራሚ እውነት ደግሞ ከህፃኑ እድገት ጋር የጡት ወተት ንጥረ ነገሮች ቅንብር ይለዋወጣል፡፡
ታምኛለሽ? ከጊዜው ቀድሞ የተወለደ ህፃን የሚያገኘው የጡት ወተት በጊዜው ከተወለደ ህፃን ከሚያገኘው የተለየ ነው። ከጊዜው ቀድሞ የተወለደ ህፃን የሚያገኘው በፕሮቲንና የጉልበት መጠን (calories) ከፍ ያለ ነው። ለእድገት የሚያስፈልገውን እንዲያገኝና በፍጥነት የሚገባው እድገት ላይ እንዲደርስ፡፡
በቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ውስጥ የእናት ጡት ወተት የበለጠ ስብ አለው። በሞቃታማ የአየር ጠባይ ውስጥ ደግሞ ብዙ ውሃ ይይዛል፡፡ ልጅሽ በጣም ከተራበ በጣም ጠንከር አድርጎ ስለሚጠባ ቅባት ያለው ወተት ያገኛል፡፡ እንዲሁ በተጠማ ጊዜ የበለጠ ዘና ብሎ ስለሚጠባ ዝቅተኛ ካሎሪ ያለው ውሃ የበዛበት ወተት ያገኛል፡፡ ሰውነታችን እንዴት እንደሚሰራ አያስገርምም?
የጡት ወተት ለሰው ልጆች ብቻ የተለየ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡
ልክ የሌሎቹ አጥቢ እንስሳት ወተት ለልጆቻቸው ልዩ ሆኖ እንደተዘጋጀው፡፡ የሰው ወተት ለሰው ልጆች የተለየ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡
ለምሳሌ የላም ወተት በፕሮቲን ፣ በማዕድናት ፣ እና በእድገት ሆርሞን የተሞላ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥጃው (የላሟ ልጅ) ከተወለደ በኃላ በሰዓታት ውስጥ መነሳት እና በራሱ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የጡንቻ እና የአጥንት እድገት ለህልውናቸው አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
ለሰው ልጆች ግን አንጎል ለህልውናችን ዋና አካል ነው፡፡ የሰው ወተት የአንጎልን እድገት በሚያሳድጉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የተሞላ ነው፡፡
ለዚያም እንደሆነ አምናለሁ በአንድ ጥናት ላይ ጡት የጠቡ ሕፃናት በአይኪው (IQ) ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያሳዩት፡፡
ጡት የጠቡ ህፃናት የጆሮ መመርቀዝ (ኢንፌክሽን) ፣ ጉንፋን ፣ ተቅማጥ ፣ እና የሆድ ድርቀት በጭራሽ አይኖራቸውም ወይም በብዛት አይዛቸውም፡፡
ይህ ጥናት የአንድ ወር ብቻ ጡት ማጥባት የጆሮ ኢንፌክሽን እድልን በ4% እንደሚቀንስ ያሳያል፡፡ ለስድስት ወራት ጡት መጥባት ደግሞ የጆሮ ኢንፌክሽንን በ17% ይቀንሳል፡፡
እንዲሁም በዚህ ጥናት መሠረት ጡት ማጥባት የጉንፋን ህመምን ክብደት ይቀንሳል፡፡
እዚህ ላይ የራሴን ልምድ እንደ ማስረጃ ላካፍል፡፡
ልጃችን ከአንድ ዓመት በላይ ጡት በመጥባት ላይ ነው፡፡ እናም በጭራሽ ምንም ዓይነት ኢንፌክሽን ፣ ጉንፋን ፣ ተቅማጥ ፣ ወይም የሆድ ድርቀት አጋጥሞት አያውቅም፡፡
አንድም ቀን ወደ ድንገተኛ ክፍል ሮጠን አናውቅም ወይም የኢንፌክሽን መድሃኒት (antibiotics) መውሰድ አስፈልጎት አያውቅም፡፡ ምንም እንኳን ዘወትር በመሬት ላይ እንዲጫወት ብንፈቅድለትም እንዲሁም በ10 ወር ዕድሜው ወደ ኢትዮጵያ ስንጓዝ ያጋጠመው የአካባቢ ለውጥ ቢኖርም፡፡
ጡት ማጥባት ከመጠን በላይ ውፍረት እና በስኳር በሽታ የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡ (ምንጭ).
ጡት የጠቡ ሕፃናት ከጊዜ በኋላ በሕይወታቸው ውስጥ ከመጠን በላይ ውፍረት እና በስኳር በሽታ የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ (ምንጭ)
የዱቄት ወተት ሰው ሰራሽ ነው። በተጨማሪ የጡት ወተት ፍሰት ህፃኑ በሚጠባው ልክ የተወሰነ ነው። ስለዚህም ህፃኑ ሲጠግብ መጥባቱን ማቆም እንዳለበት በቀላሉ ይማራል። ነገር ግን ጡጦ ቀላል ፍሰት ስላለው ህፃኑ በአጠባቡ የመቆጣጠር ችሎታው ይቀንሳል። በዚህም ምክንያት የህፃኑን ሆድ እንዲሰፋ ያደርገዋል።
ጡት ማጥባት የድንገተኛ የህፃናት ሞት (SIDS) ይቀንሳል፡፡
ይህ ጥናት እንደሚያሳየው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ የድንገተኛ የህፃናት ሞት ጡት በሚጠቡ ሕፃናት ላይ በግማሽ ቀንሷል፡፡
ጡት ማጥባት የእናት እና የልጅ ትስስርን ያጠናክራል፡፡
አንድ ህፃን ጡት በሚጠባ ጊዜ ከእናቱ ጋር አካል ለአካል መነካካቱ በህፃኑ እና በእናቱ መካከል መተማመን እና ፍቅርን ይገነባል፡፡
ይህ ጥናት ጡት የሚጠቡ ህፃናት ችግሮችን ወደ ውስጣቸው የማስገባት ዕድላቸው ዝቅተኛ እና በህይወታቸውም በብዛት በድብርት እንደማይሰቃዩ ያሳያል፡፡
ይሄ በምንም መንገድ እናቶች በጡጦ ከሚመገቧቸው ህፃናት ጋር ትስስር መፍጠር አይችሉም ለማለት ሳይሆን ጡት ማጥባት መመገብ ብቻ ሳይሆን ለህፃኑ ምቾት ሰጪ መሆኑን ለመግለፅ ነው።
በመጨረሻም እኔ ጡት ለማጥባት በመምረጤ እንድሸማቅ እና እንዳፍር እንድደረግ እንደማልፈልገው ሁሉ ፤ ለልጆቻቸው የዱቄት ወተት (ፎርሙላ) ለመመገብ የወሰኑ እናቶችን ለማሸማቀቅ ወይም ለማሳፈር በጭራሽ ፍላጎት የለኝም፡፡
ሙሉ በሙሉ የግል ምርጫ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ለአንዳንዶች የዱቄት ወተት (ፎርሙላ) መመገብ በህክምና አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ወይም የጡት ወተት አቅርቦት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ለመረጃ ብቻ ነው። እናም ልጅሽን ጡት ለማጥባት ወይም አለማጥባት ውሳኔ ለመወሰን እያሰብሽ እንደሆነ ወይም ጡት እያጠባሽ ስለማጥባት ጥቅሞች ለማወቅ ካስፈለገሽ አንድ ነገር ይሰጥሻል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የበለጠ ስለ ጡት ማጥባት ጠቃሚ ምክሮች ማግኘት ከፈለግሽ ይህን ፅሁፍ አንብቢ።
መረጃው ጠቃሚ ሆኖ ታገኝዋለሽ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ፡፡ እንደ እኔ ጡት ታጠቢያለሽ? በልጅዎ ላይ ያየሻቸው ጥቅሞች ምን ምን ናቸው? ከዚህ በታች ባለው አስተያየት መስጫ ውስጥ አሳውቂኝ፡፡
ምንጭ:-
- TexasWIC.org
- https://www.healthychildren.org/English/ages-stages/baby/breastfeeding/Pages/default.aspx
- https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/infant-and-young-child-feeding
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC3586783/
- https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/6798576/
- https://jamanetwork.com/journals/jamapsychiatry/fullarticle/482695
- https://www.sciencedaily.com/releases/2016/05/160524123440.htm
- https://www.aap.org/en-us/professional-resources/Research/Pages/Breastfeeding-Fully-for-6-Months-vs-4-Months-Decreases-Risk-of-Respiratory-Tract-Infection.aspx
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC4374721/
- https://pediatrics.aappublications.org/content/123/3/e406
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC3916850/
Mihret Tesfaye
Haniye this is really educational keep doing what you are doing!!!
ሐና ኃይሌ
Thank you, Miri.
More content about motherhood, and baby care are coming, keep coming to EnatHood blog 🙂
Hiwot
What an informative article Hanniyee. This is the topic I love to talk about when I meet soon to be moms. I share my breastfeeding journey with them.Breastfeeding was the best decision I made when I had my daughter. I enjoyed every moment of it☺️
ሐና ኃይሌ
Oh Thank you Hiwi.
You’re one advocate of breastfeeding. Keep spreading the amazing benefits of breastfeeding!!
I love breastfeeding and I am so grateful I able to breastfeed my son too.
Rahwa
Thank you so much dear ❤️
ሐና ኃይሌ
You’re welcome Rahwa.
I am glad you like the content.