እንኳን ደስ አለሽ ማማ!! የጡትሽን ወተት መጠን መጨመር አስፈልጎሻል? ወይም እርጉዝ ነሽ እናም በቅድሚያ ስለ ጡት ማጥባት መማር ትፈልጊያለሽ።
የጡትሽን ወተት መጠን መጨመር አስፈልጎሻል፡፡ ወይስ እርጉዝ ነሽ እናም በቅድሚያ ስለ ጡት ማጥባት መማር ትፈልጊያለሽ?
ለማንኛውም… አለሁልሽ!! እኔም በአንድ ወቅት በአንቺ ቦታ ነበርኩ። እዚህ የምታገኝው መረጃ ያበረታሻል ፣ ከመነሻው በጣም ጥሩ ጡት የማጥባት ግንኙት እንድትመሰርቺ ያግዝሻል ፣ ወይም ለተወሰኑ ጥያቄዎችሽ መልስ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ጡት ማጥባት እጅግ አስደሳች ነው።
በጣም ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለልጅሽም ሆነ ለራስሽ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡
ስለ ጥቅሞቹ ወደ በኋላ ላይ በጥልቀት እንነጋገራለን። ነገር ግን ጡት ማጥባት በመጀመሪያዎቹ ቀናት እንዲያውም ለሳምንታት ከባድ ሊሆን እንደሚችል አልክድም፡፡
አስታውሳለሁ እኔም ተስፋ ልቆርጥ ትንሽ ነበር የቀረኝ ግን እንደምንም እኔ እና ልጄ በራሳችን ገብቶንና ተግባብተን ጡት ማጥባቴን ቀጠልኩ፡፡ አሁን በጣም አመሰግናለሁ ተስፋ ቆርጬ ባለማቆሜ፡፡ ከአንድ አመት በላይ ሆኖኛል አሁንም ጡት እያጠባሁ ነው፡፡ ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንኩ መገመት ይከብዳል፡፡ ለልጄም ሆነ ለራሴ ያለውን ጥቅም አይቼዋለሁ፡፡
ስለዚህም ስለ ጠቃሚ የጡት ማጥባት ልምዶች ፣ ስለ እራሴ ተሞክሮ ፣ እና በአጠቃላይ ስለ ጡት ማጥባት ማወቅ ስለሚፈልግሽ ነገሮች ሁሉ እንነጋገር፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ሰውነትሽ ጡት ለማጥባት የተዘጋጀ ነው፡፡
ማማ ጡት የማጥባት ችሎታሽን በጭራሽ አትጠራጠሪው!!
በእርግዝና ወቅት ሰውነትሽ ጡት ለማጥባት ይዘጋጃል፡፡ ሳይንስ እንደሚለው በ4ኛው ወር እርግዝናሽ ላይ ጡትሽ ለልጅሽ የመጀመሪያ ወተት እንገር (colostrum) ማምረት ይጀምራል፡፡
ይህ እውነት መሆን አለበት ምክንያቱም እርጉዝ እያለሁ ከ6-7 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ጡቴ እንገር ማምረት እንደጀመረ አስተውያለሁ፡፡ እንገር አንዳንድ ሰዎች ወርቃማ ወተት ብለው ይጠሩታል ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ቀለሙ ቢጫ ስለሆነ ነው፡፡ ለልጅሽ ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ቀናት በጣም አስፈላጊው ምግብ ነው፡፡
እንገር የህፃናትን የበሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ያደርጋል፡፡
በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን (antibodies) ስለሚይዝ ቀደም ብለሽ ለልጅሽ ተፈጥሯዊ ክትባት እንደመስጠት ነው፡፡ በተጨማሪም እንገር ሆድን የማለስለስ ችሎታ ስላለው ህፃኑ እንዲፀዳዳ ይረዳዋል፡፡ በተለይም የመጀመሪያው እንደ ሬንጅ የመሰለ ጥቁር ቆሻሻ (meconium) ለማስወፈድ ይረዳል። ይህ ቆሻሻ ህፃኑ ከመወለዱ በፊት በሆዱ ውስጥ የሚከማች ነው፡፡ በተጨማሪም እንገር በወፍ በሽታ (jaundice) የመያዝ እድሉን ዝቅ ያደርገዋል። የወፍ በሽታ የህፃናትን ቆዳ እና አይኖች ቢጫ የሚያደርግ ነው፡፡
የጡት ማጥባት ጥቅሞች
ጡት ማጥባት የሚያስገኘው ጥቅም በአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ (AAP) እና በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በሚገባ የተመሰከረለት ነው፡፡
ሁለቱም AAP እና WHO ህፃኑ ከተወለደ በኋላ በ1 ሰዓት ውስጥ ጡት መጥባት እንዲጀምር ፣ ለ6 ወራት ጡት ብቻ እንዲጠባ ፣ እና ቢያንስ ለ1 ዓመት ያህል ወይም እስከተቻለው ድረስ ጡት መጥባቱን እንዲቀጥሉ ይመክራሉ፡፡
እንዲሁም ብዙ ጥናቶች እየወጡ የጡት ማጥባትን ጥቅሞች እያረጋገጡ ናቸው፡፡ እስኪ ከዚህ በታች የጡት ማጥባትን ጥቅሞች አንድ በአንድ እንመልከት።
ጡት ማጥባት ለህፃናት ያለው ጥቅም
የእናት ጡት ወተት ፍጹም ጥሩ ሆኖ የተዘጋ ፣ የተሟላ ምግብ ፣ እና የህፃኑን የአመጋገብ ፍላጎቶች ለማርካት በመደበኛነት የሚለዋወጥ ነው፡፡
የእናት ጡት ወተት ህፃኑ ለማደግ የሚያስፈልገውን ስብ ፣ ካርቦሃይድሬት ፣ ከውሃ ፣ እስከ ሆርሞኖች ፣ እና በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን አቀናብሮ ይይዛል፡፡
አስገራሚ እውነት ደግሞ ከህፃኑ እድገት ጋር የጡት ወተት ንጥረ ነገሮች ቅንብር ይለዋወጣል፡፡
ታምኛለሽ? ከጊዜው ቀድሞ የተወለደ ህፃን የሚያገኘው የጡት ወተት በጊዜው ከተወለደ ህፃን ከሚያገኘው የተለየ ነው። ከጊዜው ቀድሞ የተወለደ ህፃን የሚያገኘው በፕሮቲንና በሚሰጠው የጉልበት መጠን (calories) ከፍ ያለ ነው። ለእድገት የሚያስፈልገውን እንዲያገኝና በፍጥነት የሚገባው እድገት ላይ እንዲደርስ፡፡
በቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ውስጥ የእናት ጡት ወተት የበለጠ ስብ አለው። በሞቃታማ የአየር ጠባይ ውስጥ ደግሞ ብዙ ውሃ ይይዛል፡፡ ልጅሽ በጣም ከተራበ በጣም ጠንከር አድርጎ ስለሚጠባ ቅባት ያለው ወተት ያገኛል፡፡ እንዲሁ በተጠማ ጊዜ የበለጠ ዘና ብሎ ስለሚጠባ ዝቅተኛ ካሎሪ ያለው ውሃ የበዛበት ወተት ያገኛል፡፡ ሰውነታችን እንዴት እንደሚሰራ አያስገርምም?
የሰው ወተት ለሰው ልጆች የተለየ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ልክ የሌሎቹ አጥቢ እንስሳት ወተት ለልጆቻቸው ልዩ ሆኖ እንደተዘጋጀው፡፡
ለምሳሌ የላም ወተት በፕሮቲን ፣ በማዕድናት ፣ እና በእድገት ሆርሞን የተሞላ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥጃው (የላሟ ልጅ) ከተወለደ በኃላ በሰዓታት ውስጥ መነሳት እና በራሱ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የጡንቻ እና የአጥንት እድገት ለህልውናቸው አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
ለሰው ልጆች ግን አንጎል ለህልውናችን ዋና አካል ነው፡፡ የሰው ወተት የአንጎልን እድገት በሚያሳድጉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የተሞላ ነው፡፡
ለዚያም እንደሆነ አምናለሁ በአንድ ጥናት ላይ ጡት የጠቡ ሕፃናት በአይኪው (IQ) ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያሳዩት፡፡
ጡት የጠቡ ህፃናት የጆሮ መመርቀዝ (ear infections) ፣ ጉንፋን ፣ ተቅማጥ ፣ እና የሆድ ድርቀት በጭራሽ አይኖራቸውም ወይም በብዛት አይዛቸውም፡፡
ይህ ጥናት የአንድ ወር ብቻ ጡት ማጥባት የጆሮ ኢንፌክሽን እድልን በ4% እንደሚቀንስ ያሳያል፡፡ ለስድስት ወራት ጡት መጥባት ደግሞ የጆሮ ኢንፌክሽንን በ17% ይቀንሳል፡፡ እንዲሁም በዚህ ጥናት መሠረት ጡት ማጥባት የጉንፋን ህመምን ክብደት ይቀንሳል፡፡
በድጋሚ የእንገር ወተት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ለመገንባት የሚያግዙ ብዙ ቁጥር ያላቸውን በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ ታውቋል፡፡ (ምንጭ)
እዚህ ላይ የራሴን ልምድ እንደ ማስረጃ ላካፍል፡፡ እንደተናገርኩት ልጃችን ከአንድ ዓመት በላይ ጡት በመጥባት ላይ ነው፡፡ እናም በጭራሽ ምንም ዓይነት ኢንፌክሽን ፣ ጉንፋን ፣ ተቅማጥ ፣ ወይም የሆድ ድርቀት አጋጥሞት አያውቅም፡፡
አንድም ቀን ወደ ድንገተኛ ክፍል ሮጠን አናውቅም ወይም የኢንፌክሽን መድሃኒት (antibiotics) መውሰድ አስፈልጎት አያውቅም፡፡ ምንም እንኳን ዘወትር በመሬት ላይ እንዲጫወት ብንፈቅድለትም እንዲሁም በ10 ወር ዕድሜው ወደ ኢትዮጵያ ስንጓዝ ያጋጠመው የአካባቢ ለውጥ ቢኖርም፡፡
ጡት ማጥባት ከመጠን በላይ ውፍረት እና በስኳር በሽታ የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡.
ጡት የጠቡ ሕፃናት በእድሜ ከፍ ሲሉ ከመጠን በላይ ውፍረት እና የስኳር በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ካልጠቡ ሕፃናት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው ፡፡ (ምንጭ)
ጡት ማጥባት የድንገተኛ የህፃናት ሞት (SIDS) ይቀንሳል፡፡ (SIDS).
ይህ ጥናት እንደሚያሳየው በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ የድንገተኛ የህፃናት ሞት ጡት በሚጠቡ ሕፃናት ላይ በግማሽ ቀንሷል፡፡
ጡት ማጥባት የእናት እና የልጅ ትስስርን ያጠናክራል፡፡
አንድ ህፃን ጡት በሚጠባ ጊዜ ከእናቱ ጋር አካል ለአካል መነካካቱ በህፃኑ እና በእናቱ መካከል መተማመን እና ፍቅርን ይገነባል፡፡ ይህ ጥናት ጡት የሚጠቡ ህፃናት ችግሮችን ወደ ውስጣቸው የማስገባት ዕድላቸው ዝቅተኛ እና በህይወታቸውም በብዛት በድብርት እንደማይሰቃዩ ያሳያል፡፡
ይሄ በምንም መንገድ እናቶች በጡጦ ከሚመገቧቸው ህፃናት ጋር ትስስር መፍጠር አይችሉም ለማለት ሳይሆን ጡት ማጥባት መመገብ ብቻ ሳይሆን ለህፃኑ ምቾት ሰጪ መሆኑን ለመግለፅ ነው።
ጡት ማጥባት ለእናት ያለው ጥቅም
ጡት ማጥባት ከወሊድ በቶሎ ለማገገም ይረዳል፡፡
በምታጠቢበት ጊዜ ኦክሲቶሲን (oxytocin) የተባለ ሆርሞን ስለሚለቀቅ ማህፀን እንዲሰበሰብ ያደርጋል ይህም ከፍተኛ የደም መፍሰስ እድልን ይቀንሳል እና ማህፀን ወደ ቅድመ-እርግዝና መጠን እንዲመለስ ይረዳል፡
ለዚህም ነው ከተወለደ በኋላ በመጀመሪያው አንድ ሰዓት ውስጥ ጡት ማጥባት የሚመከርረው፡፡ አሁንም ተፈጥሮ እንዴት እንደሚሰራ አያስደንቅም? እኔ ሁሌም ያስደንቀኛል!!
ጡት ማጥባት ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ድብርትን ይቀንሳል፡፡
በጡት ማጥባት ጊዜ እንደ ፕሮላክቲን (prolactin) እና ኢንዶርፊን (endorfin) ያሉ ሆርሞኖች ስለሚለቀቁ ዘና እንድትይ እና ከልጅሽ ጋር የመቀራረብ ስሜት እንዲኖርሽ ይረዳል፡፡
ሳይንቲስቶች ከወሊድ በኋላ ለድብርት መከሰት አንዱ መንስኤ የፕሮላክቲን መቀነስ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ይህ ጥናት እንደሚያሳየው ጡት ማጥባት ፕሮላክቲን በከፍተኛ መጠን እንዳይቀንስ ይረዳል።
የጡት እና የማህፀን ካንሰር የመያዝ እድልን ዝቅ ያደርጋል፡፡r
በዚህ ምርምር እንደሚያሳየው አንዲት ሴት የጡት ካንሰር የመያዝ እድሏ 7% በእያንዳንዱ ጡት ባጠባችው ህፃን ይቀንሳል። በተጨማሪ ደግሞ ለእያንዳንዱ 12 ወራት ጡት ማጥባት በ4.3% የጡት እና የማህፀን ካንሰር የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡
ጡት ማጥባት የእርግዝና ክብደትን በፍጥነት ለመቀነስ ይረዳል፡፡.
ጡት በምታጠቢበት ጊዜ በቀን ወደ 600 ካሎሪ ታቃጥያለሽ፡፡ ስለዚህም ለእኔ የእርግዝና ክብደቴን ለመቀነስ እና ጤናማ ክብደት እንዲኖረኝ ከረዱኝ ነገሮች መካከል አንዱ ጡት ማጥባት እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ጡት ማጥባት ልጅን በጡጦ ከመመገብ የበለጠ ቀላል ነው፡፡
እስቲ አስቢው የጡት ወተት ሁልጊዜ ዝግጁ ነው። ሁልጊዜም በትክክለኛው የሙቀት መጠን ላይ ነው ፣ መለካት አያስፈልገውም ፣ ማቀዝቀዣ ወይም ማሞቂያ አያስፈልገውም ፣ የጡጦ ዕቃ ማጠብ እና ማፅዳት አይጠይቅም፡፡ ምን ያህል ሥራ እንደሚቀነስ አየሽ?
በተለይ ለሊት በመኝታ ጊዜ ፣ ረጅም ጉዞ ላይ ወይም ከቤት ውጭ ስትወጪ ጡት የምታጠቢ ከሆነ ምንም መሸከም አያስፈልግሽም!!
ጡት ማጥባት ወጪን ይቀንሳል፡፡
ጡት ማጥባት ወጪን ይቀንሳል፡፡ የዱቄት ወተት ወጪ በወር በአማካይ ከ100 - 200 ዶላር ይሆናል፡፡ እንደ ህፃኑ ዕድሜ እና ክብደት መጠን ማለት ነው። የHypoallergenic (አለርጂክ ላላቸው ህፃናት የሚታዘዝ) የዱቄት ወተት ከተፈለገ ደግሞ የበለጠ ብዙ ወጪ ይጠይቃል።
ልጅሽን ከወለድሽ በኋላ የመጀመሪያው አንድ ሰዓት
ኦ ማማ ይህ ተዓምራዊ ሰዓት ነው!! ደስታሽ ጨረቃ ላይ ደርሷል፡፡ ከረጅም ዘጠኝ በላይ ወራቶች ጥበቃ በኋላ ውድ ልጅሽን አግኝተሻል፡፡ በድጋሚ እንኳን ደስ አለሽ፡፡
ህፃኑ እንደተወለደ በደረትሽ ላይ መደረግ አለበት፡፡ ተጨማሪ የሕክምና እንክብካቤ ካላስፈለገው በስተቀር ፣ አብዛኛውን ጊዜ ነርሶቹ ደረትሽ ላይ ያደርጉልሻል፡፡ ነገር ግን ነርሶቹ ልጅሽን ካላመጡ እና የራሳቸውን እንደ ክብደት መለካት ያለ ስራ ቅድሚያ የሚሰጡ ከሆነ ልጅሽን እንዲያሳቅፉሽ እና ደረትሽ ላይ እንድታደርጊ ጠይቂአቸው፡፡ ልጅሽን መገናኘት እና መያዝ ይገባሻል!!
ህፃኑ በደረትሽ ላይ ሲቀመጥ የአካል ለአካል መነካካት ይፈጠራል ይህም ልጅሽን እንዲመቸው ያደርጋል። ከዚያም ህጻኑ በተፈጥሮ ራሱ ጡትሽን እና የጡትሽን ጫፍ መፈለግ ይጀምራል፡፡
ልጅሽ ወደ ጡትሽ ሲሳብ እና ለመጥባት ሲሞክር መመልከቱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ህፃኑ በራሱ ፍላጎት ካላሳየ የጡትሽን ጫፍ እንዲነካው ፣ እንዲያሸተው ፣ እና እንዲቀምሰው ለመርዳት ሞክሪ፡፡ ህፃኑ አሁንም ፍላጎት ካላሳየ እርዳታ ጠይቂ።
በህፃኑ የመጀመሪያው የህይወቱ አንድ ሰዓት ውስጥ ጡትሽን ማስተዋወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ጡትሽ ወተት እንዲያመርት ያደርጋል። ይህም ለወደፊት የወተት አቅርቦት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲኖርሽ ያደርጋል፡፡
በተቻለ መጠን የእንጀራ እናት (pacifier) እና ጡጦ አስወግጂ። ልጅሽን ግራ ሊያጋባ ስለሚችል እና እንዴት ጡትሽን በአፉ መያዝ እንዲሁም መጥባት እንዳለበት ለመማር አስቸጋሪ ይሆንበታል።
እንደ አጠቃላይ መመሪያ ህፃኑ 3 ወር አካባቢ ሲሞላው እና ጡት ማጥባት በጥሩ ሁኔታ ከቻለ በኋላ የእንጀራ እናት እና ጡጦ መስጠት ይመከራል፡፡
እኔ ልጄን በወለድኩ ጊዜ በደረቴ ላይ ለማድረግ አካል ለአካል ለመገናኘት እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ እንዳልኩት አስገራሚ ነው እንዴት ልጄ ወዲያውኑ ወደ ደረቴ መጎተት እንደጀመረ እና ጡት ለመጥባት እንደሞከረ፡፡
ከተወለደ በመጀመሪያው ሰዓት ውስጥ ጡት መጥባት ስለጀመረ በወተት አቅርቦት አልተቸገርኩም፡፡ ልጄ የእንጀራ እናት እና ጡጦ ስላልተሰጠው ግራ አልተጋባም፡፡ በጣም ጥሩ ጅማሪ ነበር!!
የእኔ የጡት ማጥባት ትግል በኋላ ላይ ነው የመጣው። እርሱም የጡት ማጋት እና በወተት መወጠር (engorgement) ፣ ልክ ባልሆነ አጠባብ ምክንያት የቆሰለ የጡት ጫፎ ፣ ከመጠን በላይ የወተት አቅርቦት ፣ እና የፈንገስ ኢንፌክሽን (thrush) ናቸው፡፡ ማንበብሽን ቀጥይ ፣ ስለ ሁሉም አንድ በአንድ እንነጋገራለን፡፡
ልጅሽ ጡትሽን በትክክል እንዲይዝና ለመጥባት እንዲችል እንዴት መርዳት ትችያለሽ?
- ከወለድሽ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ሰዓታት ውስጥ ጡት ለማጥባት ሞክሪ፡፡ ጡት ለማጥባት ምቹ የሆነ አቀማመጥ ምረጪ። ለድጋፍ ትራሶችን መጠቀም ትችያለሽ፡፡
- ልጅሽን አቅፈሽ ወደ ሰውነትሽ አስጠጊ፡፡ አፍንጫው ከጡትሽ ጫፍ ጋር እንዲስማማ የልጅሽን ጭንቅላት በእጅሽ ደግፊ፡፡ የልጅሽን አፍንጫ እና የላይኛውን ከንፈር የጡትሽን ጫፍ ማስነካት፡፡ ይህም ልጅሽን አፉን እንዲከፍት ይረዳዋል።
- አፉ በሰፊው እስኪከፈት ድረስ ጠብቂ
- አፉ ሲከፈት በተቻለ መጠን ብዙ ጡት በአፉ እንዲይዝ በፍጥነት ወደ ጡትሽ ጫፉ አስጠጊ ይህም በጥልቀት ጡትሽን እንዲያዝና እንዲጠባ ይረዳል፡፡
- በጥልቀት ጡትሽን በአፉ ከያዘ አፉ በሰፊው የተከፈተ ነው፡፡ ሁለቱም የልጅሽ ከንፈር ወደ ላይ ይገለበጣል እንጂ ወደ ውስጥ የታጠፈ አይሆንም፡፡
ከፍተኛ የመጎተት ህመም ወይም መቆንጠጥ ከተሰማሽ መጥባቱን ለማቋረጥ ጣትሽን ወደ አፉ ጥግ አንሸራተሽ አስገቢና መጥባቱን አቋርጪ እናም እንደገና ደግመሽ ሞክሪ። ጥሩ ምቹ የጡት ማጥባት ለማስጀመር ደጋግሞ መሞከር ሊያስፈልግ ይችላል።
ልጅሽ ጡት በትክክል እየጠባ መሆኑን እንዴት ማወቅ ትችያለሽ?
- የመጥባት ድምፅ ትሰሚያለሽ ወይም ልጅሽ ሲውጥ ታያለሽ።
- አንዴ ልጅሽ በትክክል የጡትሽን ጫፍ ከያዘና መጥባት ከጀመረ ከፍተኛ የህመም ስሜት አይሰማሽም፡፡ ረጋ ያለ የመጎተት ስሜት የተለመደ ነው። ከፍተኛ ህመም የተሳሳተ አጠባብ ምልክት ነው።
- የህፃኑ የመጥገብ ምልክት ማሳየት። ምልክቶቹም:- ጡትሽን እና የጡትሽን ጫፍ በራሱ መልቀቅ ፣ እንቅል መተኛት ፣ እጅ እና ሰውነት ዘና ማለት ናቸው።
ልጅሽ በቂ የሆነ ወተት ማግኘቱን እንዴት ማወቅ ትችያለሽ?
በአጠቃላይ አንድ ህፃን መመገብ ያለበት በቀን ከ8-12 ጊዜ ጡት በመጥባት ነው። ይህም 1 ወይም 2 የሌሊት ጡት መጥባት ጨምሮ ነው።
ነገር ግን ጡት ማጥባት እንደ በጡጦ ያለ ወተት ለመለካት ስለማይቻል ህፃኑ በቂ የሆነ የጡት ወተት ማግኘቱን ለማወቅ ዋናዋና ምልክቶችን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከእነዚህ ምልክቶች አንዳንዶቹ :-
- ህፃኑ ከጠባ በኋላ የተረጋጋ እና የጠገበ ይመስላል። ልጅሽ በራሱ ጡትሽን ከለቀቅ ፣ ዘና ብሎ ከተኛ ፣ ምናልባትም ጥሩ ጠብቷል ማለት ነው።
- ጡትሽ ከማጥባትሽ በፊት ሙሉት ያለ ነው ካጠባሽ በኋላ ይቀንሳል።በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጡትሽ የሚያመርተው እንገር ነው። ከዚያ ወደ ወተት ይቀየራል ከዛም ጡትሽ የተለየ ስሜት ይኖረዋል። ሞቃታማ ፣ ሞላ ያለ ፣ እና ተለቅ ያለ ይሆናል። ስለዚህም ከማጥባትሽ በፊት እና በኋላ በጡትሽ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት ቀላል ይሆንልሻል፡፡
- ህፃኑ የተጠቀመውን የሽንት ጨርቅ (ዳይፐር) መከታተል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት የህፃኑ ሰገራ ጥቁር ሬንጅ (ሜኮኒየም) ቀለሙ በቀስታ ወደ አረንጓዴ ይለወጣል እና በ4 - 5ተኛ ቀን ህፃኑ መደበኛ “የወተት ቅዘን” ሊኖረው ይገባል። ቢጫ ትናንሽ ፍሬ የመሠለ ነው፡፡ ለመጀመሪያው ወር በቀን 4 ወይም ከዚያ በላይ እርጥብ የሽንት ጨርቅ እና 4 ወይም ከዚያ በላይ የቅዘን የሽንት ጨርቅ ወይም በአጠቃላይ ወደ 10 የሽንት ጨርቅ መቁጠር አለብሽ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ህፃኑ በሳምንት ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ሊቀዝን ይችላል።
- የህፃኑን ክብደት መከታተል።ልጅሽ የሚመገበው በቂ ስለመሆኑ ለማወቅ የክብደት መጠን መከታተል ከሁሉም የተሻለ መንገድ ነው፡፡ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ክብደታቸውን ይቀንሳሉ፡፡ ልጅሽ የተወለደበትን ክብደት በ10-14 ቀናት ውስጥ እንደገና መመለስ አለበት። ከወሊድ በኋላ የተወለደበትን ክብደት እና ከ24 - 48 ሰዓታት ውስጥ ከሆስፒታል ስትወጪ ያለውን ክብደት በማስታወሻ ይዘሽ ህጻኑ በ 2 ሳምንቶች ውስጥ ወደ ተወለደበት የክብደት መጠን መመለሱን አረጋግጪ፡፡ ይህን በ2ተነኛ ሳምንት የህክምና ክትትል ቀጠሮሽ ላይ ከጤና ባለሙያ ጋር መነጋገርም ይቻላል።
ማማ ከዚህም በተጨማሪ ልጅሽን አስተውይ ፣ የእናትነት ውስጣዊ ጥበብሽን ተጠቀሚ ፣ እና ልብሽን አድምጪ። የሆነ ነገር ልክ ካልሆነ ታውቂያለሽ። እንዲሁም ከሐኪሞች ፣ ከጡት ማጥባት አማካሪዎች ፣ ወይም ከነርሶች እርዳታ በማንኛውም ጊዜ ለመጠየቅ አታመንቺ።
ለምን ያህል ጊዜ ጡት ማጥባት አለብሽ?
የጡት ማጥባት ማንኛውም መጠን ጥሩ ነው!!
ረዘም ላለ ጊዜ ጡት ማጥባት የበለጠ ጥሩ ነው፡፡
AAP (የአሜሪካ የሕፃናት ሕክምና አካዳሚ) ለመጀመሪያዎቹ 6 ወራቶች ህፃናት የጡት ወተት ብቻ (ምንም አይነት የዱቄት ወተት ሳይቀላቀል ፣ ውሃ ፣ ጭማቂ ወይም ምግብ ሳይጨመር የጡት ወተት ብቻ) እንድትመግቢ ይመክራል።
ከ 6 ወር በኋላ ምግብ ማስጀመር እና አንቺ እና ህፃኑ እስከፈለጋችሁ ድረስ ጡት ማጥባትሽን እንድትቀጥይ ያበረታታል። ማንኛውም የጡት ማጥባት መጠን ጠቃሚ ነው።
Tips for እንቅልፍ የሚያበዛ ህፃን
አንዳንድ ህፃናት ብዙ ይተኛሉ። እናም እንደ ማልቀስ ፣ አፋቸውን ከፍተው ምላሳቸውን መዘርጋት ፣ ወይም እጆቻቸውን ወደ አፉ እንደ ማምጣት ያሉ የረሃብ ምልክቶችን ብዙም አያሳዩም።
አዲስ የተወለደው ልጅሽ በ 24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 8 ጊዜ የማይጠባ ከሆነ ልጅሽን ለማጥባት ከእቅልፉ መቀስቀስ ያስፈልግሻል፡፡ ልጅሽን ከእንቅልፉ ለማንቃት እነዚን ዘዴዎች ሞክሪ:-
- የተወሰኑ የህፃኑን ልብሶች ማውለቅ
- አካል ለአካል መተቃቀፍ
- የህፃኑን የሽንት ጨርቅ መለወጥ
- የህፃኑን ፊት ፣ አፍ በቀስታ መንካት ወይም የህፃኑን ጀርባ ፣ እጆቹን ፣ እና እግሮቹን ማሻሸት፡፡
ንቅልፍ የሚያበዙ ህፃናት በ24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 8 ጊዜ እንዲጠቡ መበረታታት አለባቸው። እንዲሁም በቀን ውስጥ ለአንድ ጊዜ ከ4 ሰዓት የበለጠ ሳይነቅ እንዳይተኙ ማድረግ፡፡ በተጨማሪ በምታጠቢበት ጊዜ ልጅሽ እንዳይተኛ ነቅቶ እንዲጠባ ለማድረግ እነዚህን ዘዴዎች ተጠቀሚ:-
- ከጡትሽ ወተቱ በደንብ እንዲወጣ ጡትሽን በቀስታ ጫን ጫን ማድረግ
- መጥባቱን ሲቀንስ እና ሊተኛ ሲል ወደ ሌላኛው ጡትሽ መለወጥ ወይም አስተቃቀፍሽን መቀየር
- የህፃኑን እግር እና እጅ በቀስታ ማሻሸት
የጡት ማጋት (Engorgement) ማቅለያ ዘዴዎች
ጡትሽ በጣም ጠንካራ ፣ የሚያብጥ ፣ እና በጣም ሙቀት ካለው አግቷል (engorged) ወይም በወተት ተወጥሯል፡፡ ከብብትሽም ስር የተወሰነ ህመም ሊሰማሽ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ልጅሽ ጡትሽን ይዞ መጥባት ከባድ ሊሆንበት ይችላል።
ይህ በአጠቃላይ ልጅሽ በትክክል ጡትሽን ይዞ ሲጠባ ፣ በደንብ ወተት መጥባት ሲጀመር ፣ እና ጡቶችሽ የሚያመርቱትን የወተት መጠን በሚያስተካከልበት ጊዜ በራሱ ይስተካከላል፡፡
ነገር ግን ችግሩ ከቀጠለ እነዚህ ከታች የተዘረዘሩት ዘዴዎች እፎይታ ለማግኘት እንዲሁም መወጠሩን በቅድሚያ ለመከላከል የሚረዱ ናቸው።
- የጡትሽን ውጥረት ለመቀነስ ሞቅ ባለ ውሃ ገላሽን መታጠብ እና ጡትሽን ባዶ ለማድረግ በእጅሽ ወይም በጡት ማለቢያ ማሽን (breast pump) ለማለብ ሞክሪ።
ለእኔ በመጀመሪያዎቹ ወራት ጡቴ ሲያግትና ሲወጠር ሞቅ ባለ ውሃ ገላን መታጠብ እና በጡት ማለቢያ ማሽን ማለብ ረድቶኛል።
- በረዶ በላስቲክ ወይም በጨርቅ መያዝ
- ህፃኑ ተጨማሪ ወተት እንዲያገኝ ለማገዝ በምታጠቢበት ጊዜ ጡትሽን በቀስታ ማሸት
- ልጅሽን በተደጋጋሚ ጡት በማጥባት እና የሚጠባበትን ሰዓት ባለማሳለፍ የጡት ማጋትን ማስወገድ
የጡት ማጋት እና በወተት መወጠር የወተት ቧንቧ እንዲዘጋ ሊያደርግ ይችላል። ይህም በጡትሽ ላይ ቁስለት እና ጠጠር ያለ ቦታን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህ ሳይታከመ ከቀረ የጡት እብጠት ኢንፌክሽን (Mastitis) ወደሚባለው የጡት ኢንፌክሽን ሊያመራ ይችላል።
What is የጡት እብጠት ኢንፌክሽን (Mastitis)?
ከላይ እንደተጠቀሰው ማስታይተስ (Mastitis) የጡት እብጠት ኢንፌክሽን ነው። ምልክቶቹ በጡትዎ ላይ በሀይል የሚያም ጠንካራ ቦታ ፣ የጉንፋን የመሰለ ምልክት (ብርድ ብርድ ማለት ወይም ራስ ምታት) እና የሰውነት ሙቀት መጠን 100.4 ፋራናይት ወይም 38 ዲግሪ ሴልሺየስ ይገኙበታል።
የጡት እብጠት ኢንፌክሽን ከያዘሽ የጤና ባለሙያ ማነጋገር ይኖርብሻል። ብዙውን ጊዜ የኢንፌክሽን መድሀኒት (antibiotics) ይሰጣል። በታዘዘው መሠረት ሙሉ በሙሉ መውሰድ ተገቢ ነው።
የጡት እብጠት ኢንፌክሽን የመቀነሻ መንገዶች የሽንት ጨርቅ ከተቀየርሽ በኋላ እና ጡት ከማጥባትሽ በፊት እጅን መታጠብ ፣ የጡት ማጋትን ወይም በወተት መወጠርን መከላከል ፣ እና በቂ እረፍት ማድረግ ናቸው። በጣም የሚደክምሽ ከሆነ በጡት እብጠት ኢንፌክሽን ወይም ማስታይተስ የመያዝ እድልሽ ከፍተኛ ነው።
What is የፈንገስ ኢንፌክሽን - ትራሽ (Thrush)?
የፈንገስ ኢንፌክሽን የጡትሽን ጫፍ እንዲጎዳ ፣ እንዲቆስል ፣ እንዲቀላ የሚያደርግ እና በጡት ውስጥ ፈጣን የሆነ የሚወጋ የህመም ስሜት እንዲሰማው የሚያደርግ ነው።
በልጅሽ አፍ ውስጥ (ምላስ እና ጉንጭ) ነጭ ሽፍታ መኖሩን ፣ የማያቋርጥ የሽንት ጨርቅ ሽፍታ ወይም የምግብ ፍላጎት ማጣት ካለ አስተውይ።
የፈንገስ ኢንፌክሽን ከያዘሽ የጤና ባለሙያ እና የሕፃናት ሐኪም ማነጋገር አለብሽ። በኢንፌክሽን መድሃኒት (antibiotics) ያክማሉ።
የፈንገስ ኢንፌክሽን ለመከላከል ጡት ካጠባሽ በኋላ የጡትሽን ጫፎች ማፅዳት አስፈላጊ ነው። የኮኮናት(coconut) ዘይት እንደ የጡት ጫፍ ቅባት መጠቀሙ ሊረዳ ይችላል ምክንያቱም የኮኮናት ዘይት እንደ ፀረ-ባክቴሪያ ያለ ፀባይ ስላለው።
እንዲሁም እነዚህ ተፈጥሮአዊ መፍትሄዎች ሊረዱ ይችላሉ። የምትጠቀሚውን የስኳር መጠን መቀነስ ፣ (probiotics) ፕሮባዮቲክስ (ለህፃኑም ሆነ ለራስሽም) መውሰድ ፣ ጠቃሚ ያልሆን ምግብ (junk food) ማስወገድ ፣ እና ፀረ-ባክቴሪያ ምግቦችን በአመጋገብዎ ውስጥ መጨመር ሊረዳ ይችላል። እነዚህ የሚከተሉት ከፀረ-ባክቴሪያ ምግቦች የሚጠቃለሉ ናቸው። ነጭ ሽንኩርት ፣ እርጎ ፣ ሽንኩርት ፣ የኮኮናት ዘይት ፣ የፖም ኮምጣጤ ፣ ወዘተ።
How to Manage ከመጠን በላይ የወተት አቅርቦት ?
ከመጠን በላይ የወተት አቅርቦት መኖሩ ጥሩ የሚባል ችግር ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ስለሚችል ተከታትሎ ማስተካከል ያስፈልጋል።
በተቻለ መጠን ልጅሽን ጡት ማጥባት እና በጡት ማለቢያ ማሽን ማለብ መጠቆም የምችላቸው ብቸኛዎቹ መፍትሔዎች ናቸው።
ከመጠን በላይ የጡት ወተት ካለሽ አልበሽ ለሌላ ጊዜ ለመጠቀም ማስቀመጥ ትችያለሽ። ከ6-9 ወራት በበረዶ ማቀዝቀዣ ውስጥ ሊቀመጥ ይችላል። ቀኑን በትክክል መጻፍሽን እና በበሩ ውስጥ ሳይሆን በማቀዝቀዣው የጀርባ ክፍል ውስጥ መቀመጥሽን እርግጠኛ መሆን አለብሽ። በተጨማሪም በአከባቢሽ ለሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ ለሚገኙ ወተት ለሚያስፈልጋቸው ህፃናት ያለሽን ወተት ለመለገስ ማሰቡም ጥሩ ነው።
እኔም ለመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ከመጠን ያለፈ የወተት አቅርቦት ነበረኝ፡፡ እናም ጡቴ ማጋት (engorgement) ጀመረ። ጡቴን ማለብና ባዶ ማድረግ እንዳለብኝ አላወኩምኩ ነበር። ህፃኑ ሁሉንም የሚጠባ ይመስለኝ ነበር።
በተጨማሪም በተሳሳተ የጡት ማጥባት ምክንያት የጡቴ ጫፎች ህመም ነበራቸው። የታመሙት የጡቴ ጫፎች መሰንጠቅ ጀመረ ፣ ይህም ወደ ፈንገስ ኢንፌክሽን (Thrush) ትራሽ አመራ።
የነበርኩበትን ሁኔታ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት ትችያለሽ። የሚያፈስ ፣ ያበጠ ፣ ህመም ያላቸው ከመጠን በላይ ወተት የያዙ ጡቶች ፣ በተሳሳተ የጡት ማጥባት ምክንያት የታመሙ የጡት ጫፎች ፣ በትክክል ማጥባት እና ምቾት መስጠት ስላልቻልኩ የተበሳጨ ህፃን
በመጨረሻም ማለብ እንዳለብኝ ተማርኩ። በተለይም ጠዋት ላይ ጡቶቼ ሌሊት በጣም ስለሚሞሉ ፣ ለሊት ተነስቼ ማለብ የሚያስፈልጉኝ ቀናትም ነበሩ። እንዲሁም ከላይ እንደገለጽኩት ልጄን እንዴት በትክክል ጡት ማስያዝና መጥባት እንደሚችል እንዴት መርዳት እንዳለብኝ ተማርኩ።
ቀስ በቀስ እኔ እና ልጄ ገባን ፣ ልጄ በትክክል ጡት ማስያዝና መጥባት ጀመረ ፣ የጡቴ ጫፎች ተለማመዱ ፣ እና ሰውነቴ የወተት አቅርቦት ተስተካከለ። እንዲሁም የፈንገስ ኢንፌክሽን (Thrush) ትራሽ አከምኩት። እናም ሁለታችንም ተደሰትን። ተስፋ አለመቁረጤን ሁሌም አመሰግነዋለሁ!!
አሁን ጡት ማጥባት በጣም እወዳለሁ። በጡት ማጥባት ምክንያት ከልጄ ጋር ያለኝን ቅርበት በቃላት ለመግለጽ አልችልም።
የወተት አቅርቦትን እንዴት በተፈጥሮ መንገድ መጨመር ይቻላል??
ጡት ማጥባት የሚካሄደው በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው።
በጡት ማጥባት ላይ የሰዓት ለውጥ ማድረግና ጡት እንዳታጠቢ ወይም እንድትቀንሺ የሚያደርግ ማንኛውም ነገር የጡት ወተት አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ወደ ሥራ መመለስ ፣ የህፃኑ የመተኛ መርሃግብርን መለወጥ ወይም ምግብ ማስጀመር ያጠቃልላል።
በአቅርቦት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ሌላው ነገር ሆርሞን እና ከመጀመሪያው ጀምሮ የህፃኑ የተሳሳተ የጡት አያያዝና አጠባብ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ጥቂት ምክሮች ሊረዱሽ ይችላሉ።
- አካል ለአካል መነካካት። ልጅሽን በማቀፍ አካል ለአካል መነካካት በአቅርቦቱ ላይ ሊረዳ የሚችል እና ትስስርን የሚያጠናክር ሆርሞኖችን እንዲለቀቅ ያደርጋል።
- ደጋግሞ ማጥባት። የህፃን ጡትን መጥባት ተጨማሪ ወተት እንዲመረት ለማነቃቃት ይረዳል።
- ጡትን ለማለብ መሞከር።T ማለብም በተጨማሪ ወተት እንዲመረት ለማነቃቃት ይረዳል።
- በደንብ ምግብ መመገብ። ወተት ለማምረት ወደ ጡትሽ የሚሄደው ከምትመገቢው ምግብ ነው። ጠቃሚ ምግብ ተመገቢ እና በደንብ ፈሳሽ ነገር ጠጪ።
- በቂ እንቅልፍ ማግኘት እና ማረፍ። ይህ አዲስ ከተወለደ ህፃን ጋር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እናቶች ሲያርፉ እና ዘና ሲሉ የበለጠ የወተት ምርት እንደሚኖራቸው ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ ለመተኛት እና ለማረፍ የተቻለሽን ሁሉ ሞክሪ።
የጡት ማጥባት እገዛ የት ማግኘት ትችያለሽ? ?
- የሆስፒታል የእናት እና የሕፃናት ክፍል
- የጡት ማጥባት አማካሪ
- የጤና ክትትል ሃኪም (የማህጸን ሃኪም ወይም አዋላጅ)
- ላ ላቼ ሊግ (La Lache League) ወይም በአካባቢ ያለ የጡት ማጥባት ድጋፍ ቡድን
- ጡት ያጠባ ጓደኛ እና የቤተሰብ አባል
- መረጃን እና ምክሮችን ለማግኘት እንደዚህ ያለ ጦማር (blog) እና ሌላም መረጃ የሚገኝበት ጦማር ማንበብ
በመጨረሻም እልሻለሁ ማማ ተስፋ አትቁረጪ። ጡት ማጥባት ከቀን ወደ ቀን እየቀለለ ይሄዳል፡፡
ለልጅሽ በምታደርጊው ነገር ልትኮሪ ይገባሻል። ለልጅሽ ህይወት የተሻለውን ጅማሬ እየሰጠሽ ነው።
እነዚህ ሁሉ መረጃዎች የጡት ማጥባት ጉዞሽ ላይ እንደሚረዳሽ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ በታች በአስተያየቱ ውስጥ ለአንቺ ምን እንደረዳሽ ፣ ትልቁ ትግልሽ ወይም አስደሳች ጊዜሽ ምን እንደነበር ያሳውቂኝ። ከአንቺ ለመስማት እፈልጋለሁ!
ምንጭ:-
- INJOY የጤና ትምህርት
- texasWIC.org
- https://www.healthychildren.org/English/ages-stages/baby/breastfeeding/Pages/default.aspx
- https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/infant-and-young-child-feeding
- https://jamanetwork.com/journals/jamapsychiatry/fullarticle/482695
- https://www.aap.org/en-us/professional-resources/Research/Pages/Breastfeeding-Fully-for-6-Months-vs-4-Months-Decreases-Risk-of-Respiratory-Tract-Infection.aspx
- https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/6798576/
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC4374721/
- https://pediatrics.aappublications.org/content/123/3/e406
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC3916850/
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC5659274/
- https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC1143616/
- https://academic.oup.com/jn/article/131/11/3012S/4686704
.
[…] allows mothers to stay awake during surgery, experiencing the birth of their child and initiating breastfeeding […]